የቻይና አፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ትብብር በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና አፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ትብብር በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያሳየ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦ የቻይና አፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትብብር በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያሳየ መምጣቱ ተገለጸ።
በቻይና የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ እና የውይይት የጥናትና ትብብር ማዕከል ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ(POA) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ የቻይና የሥራ ኃላፊዎች የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የተለያዩ ዘርፎች ኮሚሽነሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የፋይናንስና አስተዳደር ዳይሬክተር ስቴቨን ካሪንጊ(ዶ/ር) የቻይና አፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ትብብር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ለሚገኝባት አፍሪካ ተጨማሪ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአፍሪካ የኢንተርኔት መሰረተ ልማትና ተደራሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ አሁን ካለው ፍላጎት አኳያ በርካታ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማሳለጥ የሃይል አቅርቦት፣ የመሰረተ ልማት እጥረትና የሰለጠነ የሰው ሃይል ውስንነቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑ ሀገራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረጉ ያለው ጥረት በገበያ ማፈላለግና በቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቻይና የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ልማትና ዲጂታላይዜሽን ላይ እያደረገች የሚገኘው አስተዋጽኦ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና ለሀገራት ምጣኔ ሃብት ዕድገት የጎላ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቻይና አፍሪካ ልማት ፈንድ የኢትዮጵያ ቢሮ ተወካይ ሊ ሺባኦ፤ ቻይና ለአፍሪካ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ድጋፍ እያደረገች መሆኑንም አንስተዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘላቂ የኃይል ልማት በመፍጠር ለዲጂታል ኢኮኖሚው የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገች መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በቻይና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አካዳሚ የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ሊዩ ዩኢ እንደተናገሩት፤ የቻይና አፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ትብብር እያደገ መጥቷል።
የቻይና ምጣኔ ሀብት ዕድገት መሠረቱ ዲጂታል መሠረተ ልማትና የኢንዱስትሪ መስፋፋት መሆኑን ጠቅሰው፤ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕድገት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ሀገራቸው ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መሰረት የሚጥሉትን የኔትወርክ የክላውድ ግንባታን በማስፋት አፍሪካን እያስተሳሰረች መሆኑን ጠቁመዋል።
ቻይናና አፍሪካ ዲጂታል ስነ ምህዳር ላይ ትብብራቸውን የበለጠ የሚያሳድጉ ፕሮጀክቶችን በጋራ እየተተገበሩ መሆኑንም አንስተዋል።
በቻይና ብሄራዊ ልማትና ለውጥ ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ትብብር ከፍተኛ ተመራማሪ ዚኢ ሊንካን(ዶ/ር)፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
በቻይና የሰው ሰራሽ አስተውሎት በፖሊሲ ተደግፎ በተለያዩ ዘርፎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፈ ኢንዱስትሪ ፈጣንና ውጤታማ መሆኑን አብራርተዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም በግብር፣ በኢንዱስትሪ አገልግሎትና በሌሎችም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት እየታየ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሀገራትን ከቻይና ጋር እያደረጉ ባለው የዲጂታል ኢኮኖሚ ትብብር የኢኮኖሚ ዕድገታቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።