የኦሮሞን ባህል እና ቋንቋ በጥናትና ምርምር በማገዝ ይበልጥ ማሳደግ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሞን ባህል እና ቋንቋ በጥናትና ምርምር በማገዝ ይበልጥ ማሳደግ የሚያስችል ተግባር እየተከናወነ ነው
አምቦ ፤ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፡-የኦሮሞን ባህል እና ቋንቋ በጥናትና ምርምር በማገዝ ይበልጥ ማሳደግ የሚያስችል ተግባር በትኩረት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድሕን የባሕል ጥናትና ምርምር ማዕከል ከኦሮሞ ምርምር ማሕበር ጋር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ የሕብረተሰቡን ባሕልና ቋንቋ በምርምር በመደገፍ የበለጠ ማሳደግ ዓላማ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል።
በዚሁ ወቅት የኦሮሞ ምርምር ማሕበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተፈሪ ቡዛየሁ (ዶ/ር )፤ የኦሮሞን ባሕል እና ቋንቋ በጥናትና ምርምር በማገዝ የበለጠ ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በተለይም የገዳ ስርዓትን ማዕከል ባደረገ መልኩ የኦሮሞን ሕዝብ ባሕልና ቋንቋ የበለጠ ለማስተዋወቅ እና ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
ዛሬ የተፈረመው ስምምነትም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ተናግረው ስምምነቱ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።
በጋራ ምርምር እና ጥናቶችን ማካሄድ፣ የምርምር ጉባኤዎችን ማዘጋጀት እና የልምድ ልውውጦችን ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።
ማሕበሩ በእነዚሕ ጉዳዮች ላይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ከሎሬት ጸጋዬ ገብረመድሕን የባሕል ጥናትና ምርምር ማዕከል በተጨማሪ ከሌሎችም ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለመስራት ማቀዱንም ገልጸዋል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን ማሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ባሕል እና ቋንቋን የሚያሳድጉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በጋራ ማከናወን እና ጥቅም ላይ ማዋል ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምነቱ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድሕን የባሕል ጥናትና ምርምር ማዕከል ይበልጥ እንዲያድግ እድል የሚፈጥርለት መሆኑን አስረድተዋል።
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ሳሙኤል ለይኩን (ዶ/ር) ፤ ከማሕበሩ ጋር የተደረገው ስምምነት ሁሉን አቀፍ የባሕል እና ቋንቋ ጥናትና ምርምር ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በባሕልና በኪነ-ጥበብ ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስምምነቱም የተጀመሩ ስራዎችን ለማፋጠን ያግዛል ሲሉ ገልጸዋል።