በቻይና እና አፍሪካ መካከል የሰው ሃይል ልማትና ቴክኖሎጂ ትብብር እየተጠናከረ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በቻይና እና አፍሪካ መካከል የሰው ሃይል ልማትና ቴክኖሎጂ ትብብር እየተጠናከረ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦ በቻይና እና አፍሪካ መካከል የሰው ሃይል ልማትና ቴክኖሎጂ ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ልማት ዲፓርትመንት ፖሊሲ ኦፊሰር ቢያትሪስ ኢጉሉ ገለጹ።
በፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (POA)፣ በቻይና የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ እና የውይይት፣ የጥናትና የትብብር ማዕከል ትብብር የተዘጋጀው የቻይና አፍሪካ ስትራቴጂክ የትብብር ዓውደ ጥናት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ልማት ዲፓርትመንት ፖሊሲ ኦፊሰር ቢያትሪስ ኢጉሉ እንዳሉት፤ ቻይና በአፍሪካ ያላት ኢንቨስትመንት ለበርካታ አፍሪካውያን ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በኢንቨስትመንቱ ከስራ ዕድል ባለፈ ቻይናዊያን ባለሙያዎች ለአፍሪካዊያን እውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዕድል እየፈጠሩ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በቻይናና አፍሪካ ግብርና ትብብር ማዕቀፍ የስልጠና መርሃ ግብር 10 ሺህ አፍሪካዊያን ባለሙያዎች በግብርና ሜካናይዜሽን፣ መስኖ ልማት፣ ግብርና ማቀነባበር ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስተዳደር ላይ ስልጠና መሰጠቱን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በብሉ ኢኮኖሚ መስክም ዘላቂ ዓሳ ሀብት ልማት ፣የውሃ ዳርቻዎች መሰረተ ልማት እና በውሃ ሀብት ልማት ላይ የአፍሪካ እና ቻይና ትብብር ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቻይናና አፍሪካ በሃይል እና ኢንዱስትሪ ልማት ላይም ያላቸው አጋርነት ሰፊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ ቢያትሪስ ገለጻ፤ እነዚህ የትብብር መስኮች በቻይና እና አፍሪካ መካከል የሰው ሃይል ልማትና ቴክኖሎጂ ትብብር እንዲጠናከር እያደረጉ ነው፡፡
በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ አቅም ግንባታ ለአፍሪካ ተቋም ዳይሬክተር ክዌንቲን ዎዶን በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የሰለጠነ የሰው ሃይል አቅርቦት እጥረት አሁንም ችግር እንደሚያጋጥም ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በአፍሪካ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በሚጠበቀው ደረጃ ስልጠናዎች ማካሄድ ላይ ባለመሰራቱ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካ አገራት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ቁጥር ዝቅተኛ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ዙሪያ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ወደ ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሚገቡ ሰልጣኞች ቁጥር እንዲጨምር ማድረግ፣ በመስኩ የማበረታቻ አሰራሮችን በመዘርጋት የዘርፉን እምቅ አቅም በተሻለ መልኩ ለመጠቀም መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞችን አቅም መገንባት፣ ለአሰልጣኞች ሳቢ የሆኑ አሰራሮችን መዘርጋት እንደሚገባ አመልክተው፤ ዘመኑ የደረሰበትን የስልጠና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በቻይና ቤጂንግጓ ኖርማል ዩኒቨርስቲ የኤጁኬሸናል ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ዲን ማ ኒንግ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ በቻይና ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) በሰፊው ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል። ይህም የትምህርት ጥራቱ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለጥናት ምርምርና ፈጠራ በግብዓትነት እያገለገለ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ተጠቃሽ ውጤቶች እየተገኙ ነው ብለዋል፡፡
ቻይና እና አፍሪካ በትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት የበለጠ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡