ቀጥታ፡

በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች ተገኝተዋል 

ጂንካ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች መገኘታቸውን የክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።


 

በክልሉ የወባ መከላከል ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል እና የፕሮግራም ዘርፍ ኃላፊ መና መኩሪያ በክልሉ በክረምት ወራት የወባ ስርጭት ከፍ ብሎ መታየቱን አንስተዋል።

ሆኖም ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የወባ ስርጭትን ለመቀነስና ለመቆጣጠር የተሳኩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል።

በክልሉ በወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞኖች የወባ ስርጭቱ ከፍ ብሎ መታየቱን ጠቅሰው፥ በእነዚህ አካባቢዎች ህብረተሰቡንና አጋር ድርጅቶችን ያሳተፈ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ በንቅናቄ መሰራቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመው በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።


 

በቢሮው የበሽታ መከላከል ዳይሬክተር ዶክተር አንተነህ ካሳዬ በበኩላቸው፤ በክልሉ በመጀመርያው ሩብ ዓመት የጤና አጋሮችን በማስተባበር የወባ ስርጭቱ ከፍ ብሎ በታየባቸው አካባቢዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ በኬሚካል የተነከረ የአልጋ አጎበር መሰራጨቱን ተናግረዋል።

በ488ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የነበሩ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና የማዳፈን ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

በተጨማሪም የወባ በሽታ ስርጭት ከፍ ብሎ በሚታይባቸው 10 ወረዳዎች የቤት ለቤት የፀረ-ወባ ኬሚካል ርጭት መከናወኑንም ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ በመጀመርያው ሩብ ዓመት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከወባ በሽታ መጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም