ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ  ለውጥ ማምጣት የሚያስችል አሰራር ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ልዩነት ያለው ለውጥ ማምጣት የሚያስችል አሰራር መሆኑን በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ሀላፊና የዘርፉ ተመራማሪ ዋጋሪ ነገሪ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ  በዚህ ዓመት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን 100 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል ።

ባለፈው ዓመት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩን አንስተው፤ በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ቁጥር 18 ማድረስ መቻሉንም  ተናግረዋል።


 

በማእከሉ የመሬት፣ ግብር፣ የንግድ ፈቃድ፣ ፓስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች እየተሰጡ መሆኑን ገልጸው በዚህም ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

ማእከሉን የማስፋት ስራ ትኩረት እንደተሰጠው ጠቁመው በቅርቡም ሦስት የአገልግሎት ማዕከላት ወደ ስራ እንደሚገቡ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ሃላፊና የዘርፉ ተመራማሪ  ዋጋሪ ነገሪ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከሚያረጋግጡ አሰራሮች መካከል ጥራቱና ተደራሽነቱ የተረጋገጠ አገልግሎት አንዱና ዋነኛው ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል መቀየራቸው የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ  መሆናቸውን አንስተዋል።

በየሀገራቱ የተመለከቱት ተሞክሮ ቀልጣፋና ሁሉንም ተጠቃሚዎች ያማከለ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያም ተግባራዊ ያደረገችው፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚበረታታና ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለአብነት የተጀመረው አገልግሎት ለዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የዜጎችን እንግልት በማስቀረት ልዩነት ያለው ለውጥ ማምጣት እንዲሁም ግልጸኝነትን በማስፈን ተጠያቂነትን በማረጋገጥ በኩል ጉልህ ሚና እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡


 

ተመራማሪው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ ይነሳ ለነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር መፍትሔ ለመስጠት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።

በተጨማሪም መሶብ የአንድ ማእከል አገልግሎት በዘርፉ የቆዩና ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በመሆኑም ከአገልግሎት ፍላጎት አንጻር ማእከላቱን የማስፋትና ተደራሽነትን የማረጋገጥ ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም