የቻይና ባለሀብቶች በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና ባለሀብቶች በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2018 (ኢዜአ)፡- የቻይና ባለሀብቶች በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያላቸው የኢንቨስትመነት ተሳትፎ እያደገ እንደሚገኝ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በአልሙኒየም ዘርፍ ለመሰማራት ከፈለጉ የቻይና ባለሀብቶች ጋር ተወያይተዋል።
ባለሀብቶቹ ከፍተኛ ሀብት በሚጠይቀው አልሙኒየም ምርት ላይ ለመሰማራት ያቀዱ ሲሆን ኮርፖሬሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ውይይቱ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎችን ያካተተ የመንግስት ልዑካን ቡድን አባላት ከባለሀብቶቹ ጋር ባለፈው ሳምንት በቻይና ካደረገው ውይይት የቀጠለ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ በለጠ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው 13 ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች እና አይሲቲ ፓርክን ጨምሮ በሶስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ200 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ተሰማርተው እንደሚገኙ ለኢዜአ ገልጸዋል።
38 በመቶ ድርሻ ከሚይዙት የውጭ ባለሀብቶች መካከል አብዛኞቹ ቻይናውያን መሆናቸውን ጠቅሰው በአልባሳት እና ጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ በዋናነት መሰማራታቸውን አመልክተዋል።
የቻይና ባለሀብቶች አዳዲስ አማራጮችን በመመልከት በአሁኑ ሰዓት በምህንድስና (ኢንጂነሪንግ) መሰማራት መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
ባለሀብቶቹ ካላቸው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ባሻገር በተለያዩ ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ስሪላንካ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ በኢኮኖሚ ዞኖቹና ፓርኮቹ ተሰማርተው ከሚገኙ የውጭ ሀገራት ባለሀብቶች መካከል እንደሚጠቀሱም አመልክተዋል።
በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑ ሀገራዊ አቅምን የሚያግዙ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየሰራ እንደሚገኝ አክለዋል።