ቀጥታ፡

ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ለልማት ስራዎች መጠናከር ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀራርበን እየሰራን ነው -የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ለልማት ስራዎች መጠናከር ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀራርበው እየሰሩ መሆኑን የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራሮች በክልሉ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሰላም እና ልማት እንዲኖር ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ለሰላምና ጸጥታ ስጋት የሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ለክልሉ መንግስት አስፈላጊ ጥቆማ እና መረጃ በመስጠት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ታፈሰ ፤ የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች በየቀበሌው ያለውን ሁኔታ በመከታተል ሰላምን ለማስፈን የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ከሰላም ጋር በተያያዘ ለውይይት የሚቀርቡ ጉዳዮች ካሲኖሩም ሀሳቦቹን በመለየት ወደ ምክር ቤቱ በማምጣት ውይይት ተደርጎበት ለመፍትሄው በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ችግሮችም ሲያጋጥሙ ለመንግስት አካላት በግልጽ በማቅረብ የሰላም እና የጸጥታ ችግሮች እየተፈቱ መሆኑን ገልጸው መንግስትም ከምክር ቤቱ የሚሰጡትን አስተያየቶች ተቀብሎ እየተገበረ መሆኑን አስረድተዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ታሪኩ ድምበሩ በበኩላቸው፤ ሰላምን በማጽናት ሂደት የፖለቲካ ተዋናዮች ድርሻ አላቸው ብለዋል።


 

የጋራ ምክር ቤቱ በተለይም የጸጥታ ስጋት ያለባቸው አካባቢዎችን በመለየት ቅድሚያ ትኩረት የሚፈልጉ እንዲሁም መሻሻል በታየባቸው ደግሞ ሰላምን ዘላቂ ከማድረግ አንጻር ከመንግስት ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምከር ቤት 22 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት የያዘ ምክር ቤት መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም