ቀጥታ፡

የሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ እየተጠናቀቀ ነው

ቁሊቶ፤ጥቅምት 27/2018 (ኢዜአ)፡- የሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የዞኑ አስተዳደር ገለፀ፡፡

የስታዲየሙን የግንባታ ሂደት በተመለከተ ለኢዜአ ማብራሪያ የሰጡት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ አቶ ከድር ቆሮቾ እንደገለፁት፤ በማህበረሰብ ተሳትፎ እየተገነባ ያለው የቁሊቶ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ግንባታ እየተፋጠነ ነው፡፡

ግንባታውን በሶስት ምዕራፎች ለማጠናቀቅ ታስቦ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑን ጠቁመው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ  እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡


 

የእግር ኳስ ሜዳውን ሰው ሰራሽ ሳር የማልበስ፤ ደረጃውን የጠበቀ የመሮጫ መምና የተመልካች መቀመጫ የመግጠም ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የቁሊቶ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተመደበለትም አስረድተዋል፡፡

የስታዲየሙ ግንባታ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት  ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ነው ያስረዱት፡፡


 

የስታዲየሙ የእግር ኳስ ሜዳውና የመሮጫ ትራኩ ግንባታ በፊፋ እና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አማካኝነት በተደረገ ምዘና  በጥሩ ሂደት ላይ  እየተከናወነ  እንደሆነ ግብረ መልስ እንደተሰጠም ገልጸዋል፡፡

ከስታዲየሙ  ግንባታ ጎን ለጎንም እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችሉ የሆቴሎች ግንባታ ለማከናወን ከባለሀብቶች ጋር መግባባት ላይ መደረሱንም ገልፀዋል፡፡


 

በሶስት ምዕራፎች ተከፍሎ ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው የሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ሐምሌ 10/2016 ዓ.ም ስራው በይፋ መጀመሩ ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም