ቀጥታ፡

ማንችስተር ሲቲ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጠባቂ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን 4 ለ 1 አሸንፏል።

ትናንት ማምሻውን በኢትሃድ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ፊል ፎደን ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አርሊንግ ሃላንድ እና ራያን ቼርኪ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ዋልዴማር አንቶን ለዶርትሙንድ ግቧን አስቆጥሯል።

ፎደን በጨዋታው ላይ ድንቅ ብቃቱን ያሳየ ሲሆን የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።

ሃላንድ ዘንድሮ በሁሉም ውድድሮች ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 18 ከፍ አድርጓል።

ድሉን ተከትሎ ማንችስተር ሲቲ በ10 ነጥብ ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ አድርጓል። 

ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በሰባት ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል።

በሌሎች ጨዋታዎች ባርሴሎና ከክለብ ብሩዥ ጋር ሶስት አቻ ተለያይቷል።


 

ጃኮብ ፎርብስ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ኒኮሎ ትሬሶልዲ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ፌራን ቶሬስ፣ ላሚን ያማል እና የክለብ ብሩዡ ክሪስቶስ ዞሊስ በራሱ ላይ ግቦቹን ለባርሴሎና ግቦቹን አስቆጥረዋል።


 

ኒውካስትል ዩናይትድ በዳን በርን እና ጆኢሊንተን ግቦች አትሌቲኮ ቢልባኦን 2 ለ 0 አሸንፏል።

በሳንሲሮ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኢንተር ሚላን ካይራት አልማቲን 2 ለ 1 አሸንፏል። ላውታሮ ማርቲኔዝ እና ካርሎስ አጉስቶ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ኦፍሪ አራድ ለካይራት ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ጋላታሳራይ አያክስን 3 ለ 0፣ ባየር ሌቨርኩሰን ቤኔፊካን እና አትላንታ ማርሴይን በተመሳሳይ 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም