ቀጥታ፡

የአፍሪካ መሪዎች ብዝሃ ህይወትን ከብሄራዊ ፖሊሲዎቻቸው ጋር ማስተሳሰር ይገባቸዋል -አምባሳደር ሳልማ ማሊካ ሃዳዲ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 27/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ መሪዎች የብዝሃ ህይወት አጀንዳን ከብሄራዊ ፖሊሲዎቻቸው ጋር በማቆራኘት ሊተገብሩ እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር አምባሳደር ሳልማ ማሊካ ሃዳዲ ገለጹ።

ከጥቅምት 23 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ በቦትስዋና ጋቦሮኒ ሲካሄድ የቆየው የመጀመሪያው የአፍሪካ የብዝሃ ህይወት ጉባኤ  በመሪዎች ደረጃ በተደረገ ስብስባ ተጠናቋል።

በጉባኤው ላይ የሀገራት መሪዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች፣ የዓለም የብዝሃ ህይወት ጥበቃ መሪዎች እና ተመራማሪዎች፣ ሀገር በቀል የማህበረሰብ መሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

“የብዝሃ ህይወትን በዘላቂነት በመጠቀም የአፍሪካን ብልጽግና ማረጋገጥ” የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር አምባሳደር ሳልማ ማሊካ ሃዳዲ ጉባኤው አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷን ለመጠበቅ በጀመረችው ጉዞ ውስጥ ታሪካዊ ሁነት መሆኑን ገልጸዋል።

ከኮንጎ ጥብቅ ደን እስከ ደቡብ አፍሪካው የኬፕ የአበባ ሀብት ቀጣና በአህጉሪቷ የሚገኙ ተፈጥሯዊ ምህዳሮች የህይወት፣ ባህል እና የኢኮኖሚ እድገት ምንጮች መሆናቸውን አመልክተዋል።


 

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ብክለት እና ዘላቂ ያልሆነ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም በአፍሪካ የብዝሃ ህይወት ላይ ስጋቶችን እንደደቀኑ ተናግረዋል።

የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ላይ የተቀናጀ የተግባር ምላሽ ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደሯ ለዘርፉ የሚያስፈልገውን መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ከአባል ሀገራት፣ ከቀጣናዊ ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ ጋር በመሆን የአፍሪካ ብዝሃ ህይወት ስትራቴጂ ከአጀንዳ 2063 እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በተጣጠመ መልኩ እንዲተገበር በትብብር እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

ብዝሃ ህይወት እንደ ተጓዳኝ ጉዳይ ሳይሆን ለአፍሪካ ሰላም፣ አይበገሬነት እና ዘላቂ ልማት ባለው ቁልፍ ድርሻ ሊታይ እንደሚገባ ጠቅሰው በዚህ ረገድም የአፍሪካ መሪዎች ብዝሃ ህይወት ከብሄራዊ ፖሊሲዎች ጋር ማስተሳሰር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ወጣቶች እና ሀገር በቀል ማህበረሰቦችን ማብቃት እንዲሁ በፋይናንስ እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዓለም አቀፍ እኩልነት ለማስፈን መትጋት ትኩረት እንደሚያሻቸው ነው ያነሱት።

የአፍሪካ ብልፅግና አረንጓዴ፣ ሁሉን አቀፍ እና ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

የጋቦሮኒው ጉባኤ የአፍሪካ ብዝሃ ህይወት ድንጋጌ ቀጣይ ለሚመጡ ትውልዶች መሰረት የሚጥል እንደሚሆንም ገልጸዋል።

ጉባኤው በአፍሪካ ብዝሃ ህይወት ሀብቶች፣ እድሎች፣ ፈተናዎችና ቀጣይ እርምጃዎች በዋናነት መምከሩን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም