በኃይማኖት ሽፋን የእርስ በርስ ግጭትና አለመተማመን እንዲፈጠር የጥፋት ተልእኮ ይዘው የሚሰሩ አካላትን በጋራ እንታገላለን - የአርሲ ዞን ኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
በኃይማኖት ሽፋን የእርስ በርስ ግጭትና አለመተማመን እንዲፈጠር የጥፋት ተልእኮ ይዘው የሚሰሩ አካላትን በጋራ እንታገላለን - የአርሲ ዞን ኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች
አዳማ ፤ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ )፦በኃይማኖት ሽፋን የእርስ በርስ ግጭትና አለመተማመን እንዲፈጠር የጥፋት ተልእኮ ይዘው የሚሰሩ አካላትን በጋራ እንደሚታገሉ የአርሲ ዞን ኃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
በአርሲ ዞን የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች እና ሃዳ ሲንቄዎችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የሰላምና የልማት ኮንፈረንስ በአሰላ ከተማ ተካሄዷል።
በኮንፈረንሱ ላይ የተሳተፉ የኃይማኖት አባቶች በኃይማኖት ሽፋን የእርስ በርስ ግጭትና አለመተማመን እንዲፈጠር የጥፋት ተልእኮ ይዘው የሚሰሩ አካላትን በጋራ እንደሚታገሉ ገልጸዋል።
የኃይማኖት አባቶቹ የዞኑ ህዝብ ለዘመናት አብሮ የኖረ፣ ጠንካራ ትስስርና ህብረት ያለው መሆኑን ጠቅሰው አሁንም በአብሮነት ትብብራችን ይጠናከራል ብለዋል።
የህዝቡን የአብሮነት እሴት ለማበላሸት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በማጋለጥ አንድነትና ሕብረትን የሚያጠናክሩ ስራዎችን እንሰራለን ሲሉም አክለዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሮባ ቱርጬ በበኩላቸው በዞኑ ሰላምን ለማደፍረስ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ በአንድነት መመከት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግስት በሁሉም አካባቢዎች ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ልማትና ዕድገትን ለማስቀጠል በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅትም የተለየ ዓላማ ያነገቡ አካላት የልማትና የዘላቂ ሰላም ግንባታ ጥረቶችን ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን እንቅስቀሴ በጋራ መታገል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የዞኑ ህዝብ በተቀናጀ መልኩ በአንድነት በመቆም ሰላሙን መጠበቅና ልማቱን ማስቀጠል እንደሚኖርበት አመልክተው በተለይም የኃይማኖት አባቶች አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአርሲ ዞን ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ጥላሁን በበኩላቸው የዞኑን ህዝብ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መልካም ጅምሮች እንዳሉ አንስተዋል።
ዞኑ የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመቻቻልና የአንድነት ምሳሌ መሆኑን አንስተው ፀረ ሰላም ኃይሎች ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ይህንን መልካም እሴት ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።
የዞኑ ሰላምና ልማት በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ህዝቡ በአንድነት በመቆም ሰላሙን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል።