በጤናው ዘርፍ አህጉራዊ ትብብርን እና ፈጠራን ይበልጥ በማስፋት የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት መሥራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በጤናው ዘርፍ አህጉራዊ ትብብርን እና ፈጠራን ይበልጥ በማስፋት የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት መሥራት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ በጤናው ዘርፍ አህጉራዊ ትብብርንና ፈጠራን ይበልጥ በማስፋት የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት መሥራት እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
ሦስተኛው ዓመታዊ የፓን አፍሪካን የቀዶ ህክምና ጤና አጠባበቅ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ፎረሙ "ከፖሊሲ ወደ ተግባር የአፍሪካን ባለብዙ-ዘርፍ የቀዶ ህክምና የሰው ኃይል ማስፋፋት" በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ፎረሙ የቀዶ ህምክና ባለሙያዎች እና ተዛማጅ የጤና ሠራተኞችን ማሰልጠን፣ ማቆየት እና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ነው የተገለጸው፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በፎረሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ እያስመዘገበች የምትገኘውን ስኬቶች በተሞክሮነት ታቀርባለች።
በተለይም በሰው ኃይል ልማት እያከናወነች የምትገኘውን ውጤታማ ስራዎች ለሌሎች አፍሪካዊያን የምታካፍልበት መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካ የቀዶ ሕክምና አጀንዳ ያላትን ጽኑ ድጋፍ ያረጋገጡት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ 2063 የልማት አጀንዳን ለማሳካት በፈጠራ እና በአብሮነት ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡
አፍሪካዊያን በጋራ በመሥራት ማንኛውም ዜጋ ሕይወት አድን አገልግሎት የሚያገኝበትና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት መረባረብ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የፓን አፍሪካ ጤና አጠባበቅ ፎረም ሊቀ-መንበር አበበ በቀለ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ የቀዶ ህክምና ሙያተኞች ቅንጅታዊ አሰራራቸውን በማጠናከር በቀዶ ህክምና ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ መፍትሔ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ፎረሙ የጋራ ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከርና በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አይነተኛ ሚና አለው ነው ያሉት።
አፍሪካዊያን በጋራ በመሥራት ማንኛውም ዜጋ ሕይወት አድን አገልግሎት የሚያገኝበትና የበለጸገች አፍሪካን ለመገንባት መረባረብ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የስማይል ትሬን ምክትል ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ንኬይሩካ ኦቢ በአፍሪካ ውስጥ የቀዶ ህክምና አገልግሎትን ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም ሊተባበር ይገባል ብለዋል፡፡
በትብብር የአህጉሪቱን የህክምና አገልግሎት ይበልጥ ማዘመን እንደሚገባ ጠቁመው፤ አፍሪካን በጋራ ለመገንባት አብሮነትን ማጎልበት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የዓለም አቀፍ የሕዝብ ድጋፍ አስተዳደር ማናጀርና የመርሲ ሺፕስ ዳይሬክተር ዶክተር ዋልት ጆንሰን አፍሪካዊያን ለጋራ ዓላማ በጋራ መስራትና መለወጥ አለባቸው ብለዋል፡፡
በህብረት በመሥራት የጤናው ዘርፍን ጨምሮ በሌሎችም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጠቅሰው ለታላቅ ድል በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
የመድረኩ ሌላኛው ዓላማ ከዚህ ቀደም የተደረሱትን የአህጉራዊ ስምምነቶች በተለይም የፓን አፍሪካን የቀዶ ህክምና ጤና አጠባበቅ 2023 ላይ የወጣው 50 ነጥብ መግባቢያ ከንድፈ ሐሳብ ወደ ተግባር ለማሸጋገር ያለመ መሆኑም ተገልጿል፡፡