ቀጥታ፡

በብሄረሰብ አስተዳደሩ ከ4 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት ስራ ተጀምሯል

ሰቆጣ ፤ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ4 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት ስራ መጀመሩን የብሄረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2018 የመስኖ ልማት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ አካሂዷል።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በብሄረሰብ አስተዳደሩ የሚስተዋለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመቅረፍ የመስኖ ልማት ዋና አቅም ነው።

በዚህም በያዝነው የበጋ ወቅት 4 ሺህ 738 ሄክታር መሬት በሁለት ዙር መስኖ በማልማት ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

በመስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥም አንድ ሺህ ሄክታር የሚሆነው መሬት በበጋ ስንዴ የሚሸፈን ሲሆን ቀሪው ደግሞ በሌሎች ሰብሎችና የአትክልት ምርቶች እንደሚለማ ተናግረዋል።

እስካሁን በተደረገው ጥረት ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን ጠቁመው ምርታማነቱን ለማሳደግ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር እየቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ በባለፈው ዓመት በመስኖ ከለማው መሬት ላይ 810 ሺህ 637 ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም