ቀጥታ፡

የጣና ሀይቅና ሀብቱ በባዮስፌር የዓለም ቅርስነት መመዘገቡ ደህንነቱ ተጠብቆ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት አስተዋጽኦ ይኖረዋል

ባሕር ዳር፤ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦የጣና ሀይቅና የውስጡ ሀብት በባዮስፌር የዓለም ቅርስነት መመዘገቡ የሀብቱ ደህንነቱን ተጠብቆ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት መፋጠን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጸ።

የጣና ሀይቅን "በተፈጥሮና ባሕላዊ ቅርስነት" ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ የሆነው ጣና በዙሪያው ያሉትን ትላልቅ ረግረጋማ ቦታዎች፣ የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎች፣ ከ217 የሚልቁ የአዕዋፍ ዝርያዎችና የተለያዩ ደሴቶች ጥንታዊ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናትም ይገኙበታል።

ይሕም ሀብት በተባበሩት መንግስታት የትምሕርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የዓለም የባዮስፌር ሪዘርቭ ተመዝግቧል።


 

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2021 በተካሄደው 41ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በየዓመቱ ጥቅምት 24 በኢትዮጵያ አቆጣጠር የዓለም የባዮስፌር ሪዘርቭ ቀን አድርጎ እንዲከበር መወሰኑ ይታወቃል።

ዘንድሮም ለ4ኛ ጊዜ ባለፈው ሰኞ መከበሩ ይታወሳል።

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጣና ሀይቅ በውስጡ 37 ደሴቶች፣ 45 የሚሆኑ ጥንታዊ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናትን በውስጡ አቅፎ የያዘ ነው።

ሀይቁ በርካታ ቀደምት የኢትዮጵያ ስልጣኔ መገለጫ የሆኑ የመንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርሶች፣ የነገስታት አጽም፣ የቀብር ቦታና እምቅ የብዝሃ ሕይወት መገኛ መሆኑን አንስተዋል።

በዩኒስኮም ሃይቁ በውስጡ ያለውን እምቅ ጸጋ በመገንዘብ በ2007 ዓ.ም በባዮስፌር ሪዘርቭ "በዓለም ብዝሃ-ሕይወት ክልልነት" መመዝገቡን አውስተዋል።

ሀብቱ በባዮስፌር የዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ደሕንነቱ በዘላቂነት ተጠብቆ እንዲተዋወቅ በማድረግ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት መፋጠን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተመልክቷል።

በሌላ በኩል የጣና ሀይቅን "በተፈጥሮና ባሕላዊ ቅርስነት" ለማስመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊው አመልክተዋል።

ቢሮው ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የጣና ሃይቅና በውስጡ ያሉትን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የመስሕብ ሃብቶች በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችል ስራ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።


 

በዚሕም አስፈላጊውን መረጃ በማሰባሰብና ተጨማሪ ጥናት በማካሄድ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ አማካኝነት ጥናቱ ተልኮ፣ በሰነድ ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት እንዳገኘ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች በተፈጥሮ ወይም በባሕል ቅርስነት ብቻ መሆኑን ጠቁመው፤ የጣና ሃይቅ ግን ተፈጥሮንና ባሕላዊ ቅርሶችን አቅፎ የያዘ በመሆኑ "በተፈጥሯዊና ባሕላዊ ቅርስነት" ለማስመዝገብ ተቀባይነት አግኝቷል ብለዋል።

በዚሕ ዓመት በደቡብ ኮሪያ በሚካሄደው የዩኔስኮ ጉባኤ ላይ የጣና ሀይቅን "በተፈጥሮና ባሕላዊ ቅርስነት" በዓለም ቅርስነት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

ቢሮው ሀይቁን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት ለማፋጠን የመንገድ፣ የጎብኚዎች ማረፊያ ቦታ፣ የጀልባ ወደቦች ግንባታ፣ የገዳማት እድሳትና ጥገናን እያከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የጣና ሀይቅ 3 ሺሕ 600 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ስፋት፣ ዘጠኝ ሜትር ጥልቀት፣ ከሰሜን ወደ ደቡብ 84 ኪሎ ሜትርና ከምስራቅ ወደ ምዕራብ 66 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም