ቀጥታ፡

በክልሉ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት እና ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት አሰራር እንዲጠናከር በቅንጅት እየተሰራ ነው

አዳማ ፤ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታትና ህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት እንዲጠናከር በተቀናጀ አግባብ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው በውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ላይ ያተኮረ ኤጀንሲዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በአዳማ አካሄዷል።


 

የቢሮ ሃላፊው አቶ አራርሶ ቢቂላ በወቅቱ እንደገለፁት በክልሉ ህገወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

በዚህም  ከፀጥታና ፍትህ አካላት እንዲሁም በዘርፉ ከተሰማሩና በክልሉ ከሚሰሩ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ኤጀንሲዎች ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ህገወጥ ስደት በዜጎች ህይወት ላይ እና በአገር ገጽታ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ ከባድ መሆኑን ጠቅሰው ዜጎችም ህጋዊ መንገድ ብቻ መከተል እንዳለባቸው መክረዋል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አቢቲ ኤዳኦ በበኩላቸው በክልሉ ህገወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለመግታት ለወጣቶች የግንዛቤ ማስረጽ ስራ እየተሰራ ነው።


 

በተለይ ወደ ተለያዩ ሀገራት በደላሎች ተታለው በህገወጥ መንገድ የሚጓዙ ዜጎች ለአስከፊ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን እንዲገነዘቡ ከማድረግ አኳያ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን የሚያከናውኑ ኤጀንሲዎች ህጋዊ አሰራርን ተከትለው እንዲሰሩ በ21 ዞኖችና በ23 ከተሞች ላይ  ክትትል፤ ድጋፍና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በቢሮው የስራ ስምሪትና የገበያ መረጃ ስርዓት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋንታዬ ታደሰ ናቸው።


 

በተለይ የፀጥታና ፍትህ አካላትን ጨምሮ ከጨፌ ኦሮሚያ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

ባለፈው በጀት ዓመት በህጋዊ መንገድ ከክልሉ 153 ሺህ ዜጎች ወደ ተለያዩ ሀገራት ለስራ መጓዛቸውንም አስታውሰዋል።

በመድረኩ ላይ ከተሳተፉ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ኤጀንሲዎች ተወካዮች መካከል አቶ ኢዘዲን አህመድ፣ በርካታ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት ለስራ በኤጀንሲያቸው በኩል መጓዛቸውን ተናግረዋል።


 

ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው ዜጎችም በህጋዊ መንገድ ብቻ በመጓዝ ከሚገጥማቸው አደጋ ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም