ቀጥታ፡

ሕብረብሔራዊ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል -  ወጣቶች    

ደሴ፤ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ ሰላም ፀንቶ  ሕብረብሔራዊ አንድነት  ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል  የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ሰልጣኝ ወጣቶች ገለጹ።  

የሰላም ሚኒስቴር ከወሎ የኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያሰለጠናቸውን የ14ኛው ዙር የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች ዛሬ አስመርቋል።


 

ከሰልጣኞች መካከል በለጠ ተረፈ በሰጠው አስተያየት፤ በቆይታቸው ስለ ሰላም፣ ስለ ብሔራዊ ጥቅም፣  አብሮነትና በጎ ፈቃድ አገልግሎት አስፈላጊነት  ዙሪያ ትምህርት ተሰጥቷቸው የተሻለ ግንዛቤ መጨበጣቸውን ተናግሯል። 

በዚህም  የሕብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል ተዘጋጅተናል ብሏል።

ሰላምን ከማፅናት ባለፈ የአቅመ ደካሞችን ቤት ለመስራት፣ አረጋዊያንን ለመንከባከብ የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል።

የአካባቢውን ባሕልና አብሮነት ለማስተዋወቅም መነሳሳቱን ነው የገለጸው።

ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ ወጣት ሀይለሚካኤል ሞላ፤  ስልጠናው ሕብረብሔራዊ አንድነታችንን ለመጠበቅና የእርስ በእርስ ትስስራችንን ለማጠናከር አግዞናል ብሏል።

ከስልጠናው ያገኘውን ግንዛቤ  በመጠቀም  ሰላምን ለማፅናት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ ሕብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን አስታወቋል። 


 

ስልጠናው ሕብረ ብሔራዊ  አንድነትን ይበልጥ በማጠናከር ለሀገር እድገት በጋራ እንዲሰሩ ያነሳሳቸው መሆኑን  የገለጸችው ደግሞ  ወጣት ኢልሃም አሊ ናት።

በበጎ ፈቃድ ከማገልገል ባለፈ ሥራ ፈጣሪና ለሥራ ተነሳሽነት እንዲኖረን ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ብላለች።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ታረቀኝ ትንታጉ (ዶ/ር) ፤ በየኒቨርሲቲው ስልጠና የወሰዱ ከአንድ ሺህ 800 በላይ ወጣቶች ዛሬ ተመርቀው አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።


 

ይህም ሀገራዊ አንድነትና ሰላም እንዲሰፍንና መስተጋብራችን እንዲጠናከር ከማገዙ ባለፈ ወጣቶች የባሕል ልውውጥና የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እንዲጎለበት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ስልጠና ዴስክ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መኮንን በበኩላቸው፤ በኢትየጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።


 

ይህንን በመገንዘብም ሚኒስቴሩ ለወጣቶች ስልጠና በመስጠት ሰላምና ሕብረብሔራዊ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር  ለማስቻል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እያሰማራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘንድሮ በአምስት ዩኒቨርሲቲዎች በሀገር ፍቅር፣ በስብዕና ግንባታ፣ በስነ ምግባር፣ በብሔራዊ መግባባትና በሥራ ዕድል ፈጠራ የሰለጠኑ ከ5 ሺህ በላይ ወጣቶች እየተመረቁ መሆኑን አንስተዋል።

በምረቃ መርሀ ግብር ላይ የፌደራል፣ የደሴ ከተማና የወሎ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችን ጨምሮ  ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም