ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ሩሲያ ግንኙነትን ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ ያለመ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 26/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነቶችን ወደ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ ያለመ ምክክር ተካሂዷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) እና የፋይናንስ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ማክሲም ኤስ ኦሬሽኪን እና ከሩሲያ የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ማክሲም ሬሼትኒኮቭ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም፥በተለያዩ ስትራቴጂካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

በተጨማሪም በዘላቂ ልማት፣ በቀጣናዊ ደኅንነት እና በጋራ ልማት ላይ መምከራቸው ተገልጿል።

ሚኒስትር ጌዲዮን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ሩሲያ በተለያዩ የትብብር ዘርፎች ላደረገችው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አመሥግነዋል።

በቀጣይም በግብርና፣በማኑፋክቸሪንግ፣ በአይሲቲ፣ በማዕድን ልማት፣ በብረታ ብረት፣ በኢነርጂ መሠረተ ልማት፣ በኑክሊየር እና ሌሎች ዘርፎች በትብብር መሥራት የሚቻልባቸው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎች መኖራቸውን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም