ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ የአካባቢውን ጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፍ የቀየረና የዲፕሎማሲ መስኩን ስኬታማ ስራ ያረጋገጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአካባቢውን ጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፍ የቀየረና የዲፕሎማሲ መስኩን ስኬታማ ተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፖለቲክስና የአፍሪካ ጥናት ማዕከል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ እና የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሪ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር ያለውን የተፈጥሮ ሀብት አልምቶ የመጠቀም ሙሉ መብት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

ምሁራኑ ኢትዮጵያ ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ በሃብቶቿ የመጠቀም መብት እንዳላት ጠቅሰው፤ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የሚደረጉ ተግባራት መጠናከር አለባቸው ብለዋል።

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሪ፤ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ፕሮጀክቶች ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስጠበቅ ባለፈ ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፖለቲክስና የአፍሪካ ጥናት ማዕከል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ይሰነዘሩባት የነበሩ ጫናዎችን ለመቋቋም ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ማከናወኗን አስታውሰዋል፡፡

በመንግስትና በዜጎች ትብብር የተከናወኑ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎች ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ሲያራምዱ የነበሩ አካላትን ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ አድርጓል ነው ያሉት።


 

ፕሮፌሰር አየለ በከሪ ኢትዮጵያ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዓለም አቀፍ ሕግን አክብራ ማጠናቀቋንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የተከተለችው አካሄድ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ያሳየ መሆኑን አመልክተው፤ ይህም ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

ግብጽ የዓባይን ወንዝ በበላይነት የመቆጣጠር ፍላጎቷ ማብቃቱን በመገንዘቧ የቀይ ባህር መድረክ የሚል ቡድን ማቋቋሟን ተናግረዋል፡፡

ግብጽ በመድረኩ በመታገዝ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ጉዳይ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳይኖራት ጥረት እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።

ይህንኑ እንቅስቃሴ ለመመከት የተጠናከሩ የዲፕሎማሲ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ነው ያነሱት።

ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአካባቢው ያለውን የጂኦ ፖለቲካዊ አሰላለፍ የቀየረና በዲፕሎማሲ መስክ የተገኘውን ድል ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞቿን ለማረጋገጥ በዲፕሎማሲው መስክ ያከናወነቻችው ተግባራት ውጤታማ እንዳደረጓት ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም