የባሌ ህዝብ ከገዳ ሥርዓት በወረሰው አስተምህሮ እና ዕሴት የተፈጥሮ ሃብቶችን በመጠበቅ አብሮ መኖርን ባህሉ ያደረገ ህዝብ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባሌ ህዝብ ከገዳ ሥርዓት በወረሰው አስተምህሮ እና ዕሴት የተፈጥሮ ሃብቶችን በመጠበቅ አብሮ መኖርን ባህሉ ያደረገ ህዝብ ነው
ሮቤ ፤ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ የባሌ ህዝብ ከገዳ ሥርዓት በወረሰው አስተምህሮ እና ዕሴት የተፈጥሮ ኃብቶችን በመጠበቅ አብሮ መኖርን ባህሉ ያደረገ ህዝብ ነው ሲሉ የአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች እና ምሁራን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ካነሱዋቸው ሀሳቦች መካከል የባሌ ህዝብ ከተፈጥሮ ሀብት ጋር ያለው መስተጋብር አንዱ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፣ “የባሌ ሕዝብ አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የጋራ የተፈጥሮ ሀብቶችን ጠብቆ በማቆየቱ ሊመሰገን ይገባል” ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዞኑ ህዝብ ያቀረቡት ምስጋናና አክብሮት የተፈጥሮ ጸጋዎችን በመንከባከብ ይበልጥ አልምቶ ለመጠቀም የሚያነሳሳ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃገር ሽማግሌዎች እና ምሁራን ገልጸዋል፡፡
ከሮቤ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ተማም ጀማል፣ በተፈጥሮ ጸጋዎች የታደለው የባሌ ዞን የበርካታ ብዝሀ ህይወት ባለቤት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የቱሪዝም መዳረሻ የሆነው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የሐረና ጥብቅ ደንና ሌሎች ውብና ማራኪ መልካም ገጽታን የተላበሰ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዳለው ጠቅሰው ፓርኩ የተለያዩ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርኩ ልማትና ብዝሀ ህይወት ጥበቃ የሰጡት ትኩረት ብሎም ለዞኑ ህዝብ ያቀረቡት ክብርና ምስጋና በታሪክ የሚታወስና ለዘላቂ ጥበቃ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ ለዘመናት ሳይለማ የተረሳው የሶፍ ኡመር ዋሻ የኢትዮጵያን ታላቅነትና መልካም ገጽታ ለአለም ህዝብ ጭምር የሚያስተዋውቅ ሌላ ቅርስ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ አማን ሐጂ አብዶ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለዞኑ ህዝብ ያቀረቡት ምስጋናና አክብሮት የተፈጥሮ ጸጋዎችንና የደን ቅሪቶችን ይበልጥ በመንከባከብ አልምቶ ለመጠቀም የሚያነሳሳ እንደሆነም አመልክተዋል።
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ ዘርፍ መምህራንም የአገር ሽማግሌዎችን ሀሳብ በመጋራት የጋራ የተፈጥሮ ሀብቶችን በመንከባከብ ለዛሬ ላቆየው የባሌ ህዝብ በመንግስት የቀረበው እውቅናና ክብር ለዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ አዎንታዊ አንድምታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በተለይም በጥብቅ ደኖች አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች በአሳታፊ የደን ልማት አስተዳደር በመደራጀት ደኑን በመጠበቅ ከስነ-ምህዳሩ ከሚያገኙት ጥቅም በተጓዳኝ ከካርቦን ሽያጭ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መምጣታቸው የጥበቃውን ተግባር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑንም ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የአካባቢ ሳይንስ ዘርፍ መምህርና ተመራማሪ ኡመር አብደላ፣ የባሌ ህዝብ ከገዳ ሥርዓት በወረሰው አስተምህሮትና ዕሴት የተፈጥሮ ኃብቶችን በመጠበቅ አብሮ መኖርን ባህሉ ያደረገ ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል ።
በተለይ የአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በቋሚ ቅርስነት መመዝገቡን ገልፀው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና በውስጡ የሚገኙ የብዝሀ ህይወት ስብጥሮች ማህበረሰቡ ጠብቆ ያቆየው ሃብት መሆኑን አመልክተዋል።
የባሌ ህዝብ የተፈጥሮ ኃብቱን በመንከባከብ ለትውልድ በማቆየቱ ከመንግሥት የተሰጠው እውቅና የጥበቃውን ሥራ ይበልጥ ውጤታማና ዘላቂ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የዘርፉ መምህርና ተመራማሪ አብዱልፈታህ አብዱ ናቸው።
የተሰጠው እውቅናም የህዝቡ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ይስተዋሉ በነበሩ ተግዳሮቶች ዙሪያ ጥናት በማካሄድ ምክረ ሀሳብ ሲለግሱ ለቆዩት የዘርፉ ምሁራንን ጭምር የሚያነሳሳ መሆኑን አስታውሰዋል።