ቀጥታ፡

ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ ናቸው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩና ቀጣናዊ ትብብርን መሰረተ ያደረገ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በሻህ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ ትብብርና የአሸናፊነት ምልክት የሆነው ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ሲመረቅ የጉባ ብስራቶችን ይፋ አድርገዋል፡፡

ሀገራዊ ፕሮጀክቶቹም የሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ማበልጸጊያ፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የቤቶች ግንባታ ናቸው፡፡

የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ በሻህ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአንድ ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ከህልውና ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምም የተመሰረተው ዳር ድንበሯን ከማስከበር፣ የግዛት አንድነቷን በማስጠበቅ፣ የዜጎቿን ተጠቃሚነት እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን በማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ብሔራዊ ጥቅም ከሉዓላዊነት ጋር ብቻ የተቆራኘ እንደነበር አስታውሰው፤ ከለውጡ ወዲህ እምቅ ሀገራዊ ሀብቶችን ለህዝብ ጥቅም በማዋል የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕዳሴ ግድብን ባስመረቁበት ወቅት ይፋ ያደረጓቸው የጉባ ብስራቶች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ሀገራዊ ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በመሰረታዊነት ከመቀየር ባለፈ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በትብብር ለማደግ ወሳኝ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከቀጣናው ሀገራት ጋር በኤሌክትሪክ ኃይልና በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር በትብብር ማደግን መሰረት ያደረገ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዳላት ያሳያሉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ጽኑ አቋም እንዳላት ያነሱት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የጀመረቻቸው ፕሮጀክቶች አዎንታዊ ተጽዕኖ ከሀገር ያለፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር የተጀመረው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ የኢትዮጵያ አርሶ አደር ምርትና ምርታማነትን በመሰረታዊነት እንደሚቀይር ገልጸዋል፡፡

የማዳበሪያ ፋብሪካው በተያዘለት 40 ወራት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን ከናይጄሪያና ሞሮኮ ቀጥሎ ሶስተኛዋ ከፍተኛ አምራች እንደሚያደርጋት ጠቅሰው፤ ከጥገኝነት በማላቀቅ እንደ ኬንያ ላሉ ሀገሮችም ማዳበሪያ ማቅረብ እንደሚያስችላት ገልጸዋል፡፡

የሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ማበልጸጊያ፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማርሽ ቀያሪ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡

የጋዝ ፋብሪካው የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ወጭ ከማስቀረት ባለፈ በራሷ አቅም ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም