ኢትዮጵያ ያጣችውን የባህር በር ባለቤትነት ለማስመለስ እያደረገች ያለውን ጥረት ያለ ልዩነት እንደግፋለን - ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ያጣችውን የባህር በር ባለቤትነት ለማስመለስ እያደረገች ያለውን ጥረት ያለ ልዩነት እንደግፋለን - ምክር ቤቱ
ወልቂጤ፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ያጣችውን የባህር በር ባለቤትነት ለማስመለስ እያደረገች ያለውን ጥረት ያለ ልዩነት እንደሚደግፉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ የመልማት፣ የደህንነት እና ታሪካዊ ባለቤትነት ጉዳይ በመሆኑ ተገቢው ምላሽ እንዲገኝ ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ይህንን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰሞኑን ተካሄዶ በነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው በመንግሥት አቋምና አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ የተደረገበትን ሁኔታ የሚገልፅ መረጃ ማግኘት አለመቻሉን አንስተዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ኢዜአ ከክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ጋር ቆይታ ባደረገበት ወቅት ኢትዮጵያ ያጣችውን የባህር በር ባለቤትነት ለማስመለስ እያደረገች ያለውን ጥረት ያለ ልዩነት በአንድ ልብ እንደግፋለን ብለዋል።
የባሕር በር ለማግኘት እየተሄደበት ያለውን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በመደገፍ አጀንዳው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉም አባላቱ አረጋግጠዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት መካከል የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ደምስ ገብሬ እንዳሉት፤ ሀገራችን ህገወጥ በሆነ መንገድ የባህር በር ማጣቷ በትውልዱ ዘንድ ቁጭት ሆኖ የኖረ ጉዳይ ነው።
ያጣነውን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ሊረባረብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በፍትሕ እና እውነታ ላይ ተመሥርታ የጠየቀችው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕጉ የሚደግፈውና ተቀባይነት ያለው በመሆኑ አጀንዳውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ሀገራችን የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋ ያለ ፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነት በመላ ኢትዮጵያውያን ተቀባይነት ያለው የሕልውና ጥያቄ ነው ሲሉ የገለፁት ደግሞ ሌላው የጋራ ምክር ቤቱ አባል ሄኖክ አብዱልሰመድ ናቸው።
የባህር በር ባለቤትነት የቅንጦት ሳይሆን ከ130 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሀገር የኢኮኖሚና የደህንነት ብሎም የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል እንዳለ ኤርጌዶ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከባሕር በር የራቀችበትን ምክንያት ለመጠየቅ የማይቻልበት ወቅት እንደነበረ አስታውሰዋል።
የባህር በር ባለቤትነት የሕልውና ጉዳይ መሆኑን በማንሳት የሀገር ዕድገትና ደህንነትን ለማረጋገጥ መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድ የሚደግፍ ነው ብለዋል።