ቀጥታ፡

የምስራቅ ዕዝ በተሰማራባቸው ግዳጆች ሁሉ በጀግንነት በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት የሀገሩ ዳር ድንበርና የሉአላዊነቷ ዘብ ሆኖ ቆሟል

ሐረር፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ በተሰማራባቸው ግዳጆች ሁሉ በጀግንነት በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት የሀገሩ ዳር ድንበርና የሉአላዊነቷ ዘብ ሆኖ መቆሙ ተገልጿል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ፤ በምስራቅ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርቶ ተልዕኮውን በላቀ ብቃት እየተወጣ ይገኛል።

በተለይም በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አሸባሪው አልሸባብ ሾልኮ በመግባት የኢትዮጵያ የልማትና የሰላም እንከን እንዳይሆን ዕዙ አስተማማኝ መከታ ሆኖ ሌት ከቀን ግዳጁን እየተወጣ መሆኑ ይታወቃል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ 305ኛ ኮር ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ኮሎኔል ማርሼት ፈለገ፤ ዕዙ በተሰማራባቸው ግዳጆች ሁሉ በጀግንነት በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት የሀገሩ ዳር ድንበርና የሉአላዊነቷ ዘብ ሆኖ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የቀጠናውን ሠላም የማረጋገጥና የምስራቁን የሀገሪቷን አካባቢዎች ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ በማድረግና ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲከናወኑ ሌት ከቀን በመቆም ተልዕኮውን በላቀ ብቃትና በቁርጠኝነት እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኮሩ አባላት በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ሀይሎችን ተከታትለው እርምጃ በመውሰድ በአካባቢው ምንም አይነት ስጋት እንዳይኖር እየሰሩ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በምስራቅ ኢትዮጵያ አገልግሎት የጀመሩ እና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ምንም አይነት መሰናክል እንዳይገጥማቸው ኮሩ በአስተማማኝ ጥበቃ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

የዕዙ የ28ኛ ክፍለጦር 2ኛ ሬጅመንት 1ኛ ሻምበል አዛዥ መቶ አለቃ ጌታሰው ጋሻው በበኩላቸው፤ዕዙ በተለይም በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አሸባሪው አል ሸባብ፣ ሌሎች የውጭ ጠላቶች ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ስጋት እንዳይሆኑ ግዳጅና ሃላፊነቱን በላቀ ብቃት እየተወጣ መሆኑን አንስተው ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የዕዙ የ27ኛ ክፍለጦር ዘመቻ መኮንን መቶ አለቃ ጌታ መሳይ ዳዊት፤ዕዙ ለሀገሩ ዳር ድንበርና ለሉአላዊነቷ መከበር በጀግንነት፣ በላቀ ብቃትና በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኤፒሲ ብረት ለበስ አዛዥ መቶ አለቃ ደጀኔ አበበ በበኩላቸው ዕዙ በምስራቅ ኢትዮጵያና በድንበር አካባቢዎች አስተማማኝ መከታ ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጣ የሚችል ትንኮሳ ካጋጠመ ፈጣንና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ የሚችል፤ በየትኛውም ስፍራ እና የአየር ሁኔታ ግዳጁን በላቀ ብቃት የሚወጣ አስተማማኝና ጠንካራ ሰራዊት ተገንብቷል ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም