ቀጥታ፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በመኽር አዝመራ በተካሄደ በርበሬ ልማት ከ720 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

ጭሮ ፣ጥቅምት 26/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በመኽር ወቅቱ ከለማው በርበሬ ከ720 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የቡና ሻይ እና ቅመማ ቅመም ልማት ቡድን መሪ አቶ ኦሉማ በዳኔ እንዳሉት በዞኑ በመኸር አዝመራ በ15 ወረዳዎች  34 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በርበሬ ለምቷል።

በዞኑ  ምርቱ በስፋት በሚካሄድባቸው የሀዊ  ጉዲና ፤ ጭሮ፤ ዳሮ ለቡ፤ ገመቺስ ፤ሀብሮ ፤ኦዳ ቡልቱም እና ቦኬ  ወረዳዎች የምርት ስብሰባ እየተካሄደ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በዚህ ዓመት ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ምርት ካለፈው ዓመት ከአስር ሺህ ኩንታል በላይ ብልጫ እንደሚኖረው ነው ያመለከቱት፡፡

በዞኑ የበርበሬ አኒሼቲቭን ለማሳካት አርሶአደሩ ልማቱን በክላስተር በማልማት በጋራ እንዲሳተፍ ስራዎች መሰራታቸውን  ተናግረዋል፡፡

አርሶአደሮች ለምርት ጥበቃና እንክብካቤ ትኩረት እንዲሰጡ በተደረገው  ድጋፍና ክትትል በሄክታር የምርታማነት መጠኑን ከ16 ኩንታል ወደ 20 ኩንታል ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን 15 ወረዳዎች እየተካሄደ ባለው የበርበሬ ልማት ከ55 ሺህ በላይ አርሶአደሮች እየተሳተፉ መሆኑም ተመልክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም