ቀጥታ፡

የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮነትን ይበልጥ በማጠናከር አበረታች ውጤት አምጥቷል - የሰላም ሚኒስቴር

ጅማ፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፡- ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮነትን ይበልጥ በማጎልበት አበረታች ውጤት ማምጣቱን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 14ኛው ዙር የበጎነት ለአብሮነት ሰልጣኝ ወጣቶች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ በጅማ ከተማ ተካሂዷል።


 

በዚህ ወቅት በሰላም ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ መብራቱ ካሳ እንደተናገሩት፤ የበጎነት ለአብሮነት ስልጠና የወጣቶችን መልካም ስነ-ምግባር በመገንባት በሀገር ፍቅር እንዲታነጹ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።

እስካሁንም ከ60ሺህ በላይ ወጣቶች ሰልጥነው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመሰማራት ያከናወኑት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮነትን ይበልጥ በማጠናከር አበረታች ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ በየተመደቡበት አካባቢ የሰላም አምባሳደሮች በመሆንና በበጎ ስራዎች ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ መፍጠር መቻላቸውንም አንስተዋል።

ወጣቶቹ የተለያዩ ቋንቋዎች በመልመድና ባሕላዊ እሴቶችን በመተዋወቅ ብዝሃነትን በማጎልበት ለብሔራዊ መግባባት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ ዙር በ5 የስልጠና ማዕከላት የተሳተፉ ከ5ሺህ በላይ ሰልጣኝ ወጣቶች ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሰማርተው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ታደሰ ሀብታሙ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጅማ ዩኒቨርሲቲ በበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ በመሳተፍ የበኩሉን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ወጣቶች ለሚወስዱት ስልጠና ጥሩ ቆይታ እንዲኖራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ከሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ተውጣጥተው ስልጠናውን የወሰዱ ወጣቶች በቆይታቸው ለህይወታቸው መሰረት የሚሆን እውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም