በክልሉ ባለፉት ሶስት ወራት በህገ-ወጥ ንግድ በተሰማሩ ከ49ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል - የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት ሶስት ወራት በህገ-ወጥ ንግድ በተሰማሩ ከ49ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል - የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ
ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በበጀት አመቱ ሶስት ወራት በህገ-ወጥ ንግድ የተሰማሩ ከ49 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ንግድ ቢሮ ምክትል ሀላፊ ተስፋዬ ገሾ ለኢዜአ እንደተናገሩት በክልሉ ህገ-ወጥ የንግድ ተግባራትን በመከላከል ጤናማ የንግድ ስርዓትን ለማስፈን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።
በበጀት አመቱ ባለፉት ሶስት ወራት ከክልሉ ፖሊስ፣ ከዐቃቤ ህግ፤ ከገቢዎችና ከትራንስፖርት ቢሮዎች የተውጣጣ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ በየዞኑና በከተሞች ሰፊ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በተሰጠው የግንዛቤ ፈጠራ ህብረተሰቡ የህገ-ወጥ ንግድ ስራ ላይ የሚያጋጥመውን ወንጀል በማሳወቅና ጥቆማ በመስጠት ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል።
በክልሉ ያለ ንግድ ፈቃድ ንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ፤ ምርትን ከባዕድ ነገሮች ጋር ቀላቅሎ መሸጥ፤ የዋጋ ዝርዝር ያለመለጠፍ የመሳሰሉ ህገወጥ ተግባራት በፈጸሙ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በተጨማሪም ሚዛን የሚያጭበረብሩ፤ ደረሰኝ የማይሰጡ፤ ያለአግባብ ምርትንና ሸቀጦችን የሚያከማቹ እና የሚደብቁ የንግድ ተቋማት ላይ ማስጠንቀቂያ የመስጠት፣ የማሸግና ሌሎች አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስዷል ነው ያሉት።
በተለይም በነዳጅ ህገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ 30 ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ የሆኑ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አምስት ሰዎች በ4 አመት እስር እንዲቀጡ መደረጉን ተናግረዋል።
ቢሮው ህገ-ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላትን ወደ ህጋዊ መስመር እንዲመለሱ የማድረጉንና ጤናማ የንግድ ስርዓት ላይ ያሉትን ደግሞ የማበረታታት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።