የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ግንባታው ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ለማውጣት የሚያስችል ነው- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ግንባታው ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ለማውጣት የሚያስችል ነው- ምሁራን
ደብረ ብርሃን፤ ጥቅምት 26/ 2018 (ኢዜአ)፡- መንግስት በብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ትግበራ ላይ ተመስርቶ እያከናወነ ያለው ተግባር ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ለማውጣት የሚያስችል ነው ሲሉ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ከፍተኛ ሚናን እየተወጣ መሆኑን ማንሳታቸው ይታወሳል።
በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ መንግስት ከግሉ ዘርፍ፣ ከህዝቡ ፣ ከአጋር አካላትና ከሲቪክ ማህበራት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት በየፈርጁ ለማፋጠን የተለያዩ ተግባራት ሲከናወን መቆየቱም ተመልክቷል።
በዚህም በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በዲጂታል ዘርፉ ላይ በትኩረት በመስራት አስደናቂ ለውጥ መመዝገቡንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ አንስተዋል።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ የእጽዋት ጥበቃ ተመራማሪ ነጋሽ ሀይሉ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹትም፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከግብርና መር ተላቆ ወደ ብዝሃ መር ኢኮኖሚ መሸጋገሩ ሁሉን አቀፍ ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል።
ይህም መንግስት ግብርናን፣ ኢንዱስትሪን፣ ቱሪዝምን፣ ማዕድንን፣ እንዲሁም ቴክኖሎጂን በማቀናጀት ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ከድህነት ለማውጣት እያደረገ ያለው ጥረት በውጤት እየታየ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ያለን ሃብትና ጸጋ በመጠቀም እድገትን ለማረጋገጥና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት በጥናትና ምርምር የመደገፍ ሚናችንን እየተወጣን እንገኛለን ብለዋል።
በተለይም የከተማ ግብርና፣ የሌማት ትሩፋት፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና ሌሎች የግብርና ልማት ስራዎች ይበልጥ ውጤታማ በመሆን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በሙያቸው እንደሚያግዙ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አዝጋሚ ከነበረው የግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ልማት ትግበራ መሸጋገሩ የሀገሪቱን እድገት በማፋጠን በአጭር ጊዜ ከድህነት ለመውጣት እንደሚያስችልም ተመራማሪው ገልጸዋል።
ከብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት አንዱ ለሆነው ግብርና የተሰጠው ትኩረት ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የአርሶ አደሩን ብሎም የሀገርን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድገው የገለፁት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ የእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አድማሱ ላቀው (ዶ/ር) ናቸው።
በዚህም የተጀመረው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ የውጪ ምንዛሬን ከማስቀረቱም በላይ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ምርትና ምርታማነትን ለማላቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ፋብሪካው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያን በተመጣጣኝ ዋጋና በሚፈልገው መጠን በማምረት ለኢንዱስትሪ ግብዓት ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማት እያከናወነች የሚገኘውን ተግባር በጥናትና ምርምር ስራዎች በማስደገፍና በውጭ ጆርናሎች እንዲታተሙ በማድረግ የመጣውን ለውጥ ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።