ቀጥታ፡

የኩላሊት እጥበት ማዕከሉ ህክምናውን በአቅራቢያችን እንድናገኝ አስችሎናል - ታካሚዎች

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ የኩላሊት እጥበት ማዕከሉ ህክምናውን በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ከማስቻሉ ባለፈ እንግልትና ወጪ እንዳስቀረላቸው ታካሚዎች ገለጹ። 

ሜሪጆይ ኢትዮጵያ በሀዋሳ ከተማ ያቋቋመው የኩላሊት እጥበት ማዕከል የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞና የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በተገኙበት በቅርቡ ተመርቆ ስራ ጀምሯል።


 

በማዕከሉ ህክምናውን እየተከታተሉ ከሚገኙት መካከል ከሻሸመኔ ከተማ የመጡት ጉተማ ገመዳ እና ከአርሲ ዞን የመጡት ሼክ ሰኢድ ሀዎ ላለፉት አራት ዓመታት የኩላሊት እጥበት ሕክምና ሲከታተሉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም ህክምናውን ለማግኘት በወረፋ ምክንያት ለእንግልትና ለተጨማሪ ወጪ ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰው፣ በቅርቡ ስራ የጀመረው የኩላሊት እጥበት ማዕከል ይህን እንግልትና ወጪ አስቀርቶልናል ብለዋል።  

ማዕከሉ ሕክምናውን በቅርበት እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ ክፍያው የታካሚዎችን አቅም ያገናዘበ መሆኑንም ጨምረው  ተናግረዋል።

በሳምንት ከሁለት ጊዜ በላይ የኩላሊት እጥበት በማድረግ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውን የገለጹት ደግሞ ከጉጂ ዞን ቦሬ የመጡት ባሪሶ ዋቆ ናቸው፡፡

በሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በሀዋሳ የተከፈተው ማዕከል ሕክምናውን በቅርበትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።


 

የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የኩላሊት እጥበት ማዕከል አስተባባሪ ኖቤል ነመራ(ዶ/ር) በበኩላቸው ማዕከሉ በዓመት 10ሺህ ዙር የኩላሊት እጥበት የማከናወን አቅም አለው ብለዋል።

የማዕከሉ መከፈት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የኩላሊት ታካሚዎች ችግር በማቃለል ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም ነው የተናገሩት፡፡

በማዕከሉ የታካሚዎችን አቅም ያገናዘበ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም የሜሪጆይ አባላትን ቁጥር በመጨመርና የበጎ አገልግሎቱን በማጠናከር ለአቅመ ደካሞች የተለየ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም