ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የትምህርት ቤት ምገባ የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስ እያገዘ ነው

አዶላ፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የትምህርት ቤት ምገባ የተማሪዎችን  መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስ እያገዘ መሆኑን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሳተና ሮቤ፤ በትምህርት ዘመኑ ከ430ሺህ በላይ ተማሪዎች ተመዝግበው የመማር ማስተማር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የትምህርት ተደራሸነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝ መጠነ ማቋረጥን ለመቀነስ ትልቅ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም በዞኑ በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር 75ሺህ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩን የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠልም ከበጎ ፈቃደኞች በተጨማሪ ከአጋር አካላት ሀብት የማሰባሰብ ስራው መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

ይህም የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሩን በማስፋት ትኩረቱን ትምህርት ላይ ያደረገ የተሻለ ትውልድ ለማፍራት የተጀመረው ስራ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አባይነህ ሸርቂቻ በዞኑ የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብርን ለማጠናከር በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር  ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ስኳርና የምግብ ዘይትን ጨምሮ ከ3ሺህ 250 ኩንታል በላይ የሚገመት የምግብ እህል ከበጎ ፈቃደኞች መሰብሰቡን ተናግረዋል።

የምገባ መርሀ ግብሩን ለማስቀጠል በህዝብ፣ በበጎ ፈቃደኞችና ባለሀብቶች የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በዞኑ የትምህርት ምገባ መርሃ ግብር እየተተገበረባቸው ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል የኦዶ ቀርሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ሲሆን የተተገበረው የምገባ መርሃ ግብር የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ መጠነ ማቋረጥ እየቀነሰ መጥቷል ያሉት የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ድሪባ ሁንዴሳ ናቸው።

የምገባ መርሀ ግብሩ የወላጆችን ጫና እየቀነሰ እና የህጻናት የትምህርት ፍላጎትን እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም