ቀጥታ፡

መንግስት የባሕር በር ማግኘትን የሕልውና ጉዳይ ማድረጉን በመደገፍ የድርሻችንን እንወጣለን

ባሕር ዳር፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፡- መንግስት የባሕር በር ማግኘትን የሕልውና ጉዳይ ማድረጉን በመደገፍ የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ የባሕርዳር ከተማ ወጣቶች እና ሴቶች ገለጹ።

ኢዜአ በባሕርዳር ከተማ ያነጋገራቸው ወጣቶች እና ሴቶች በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አጀንዳ ማድረጉ የሚበረታታና የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ሳለዓምላክ አድማሱ፤ አይነኬ የነበረው የባሕር በር ጥያቄ በለውጡ መንግስት መነሳቱ ያጣነውን መብት ለማስከበር ከፍተኛ መነሳሳትን ፈጥሯል ብሏል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ሀገር እንደመሆኗ ከባሕር በር ተገልላ የሚፈለገውን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ አዳጋች ያደርገዋል ነው ያለው።

ይህም የወጣቱን ተጠቃሚነት በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑን ጠቅሶ፤ አሁን እንደ ሀገር የተነሳው የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ በዘርፉ ኢኮኖሚ ቀጥታ የመጠቀም ተስፋችንን ያለመለመ ነው ሲል ገልጿል።

የባሕር በር አጀንዳው በፍጥነት እንዲሳካ ሰላምን ከመጠበቅ ጀምሮ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማድረግ ይገባናል ነው ያለው።

የባሕር በር አጀንዳ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉ ሀገራችን በጀመረችው መንገድ እንደሚሳካ ጥርጥር እንደሌለው የተናገረችው ደግሞ ትዕግስት አባቡ ናት።

ከውጭ ሀገራት ጋር ያለንን የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የባሕር በር ጉዳይ ወሳኝ በመሆኑ በመንግስት የተሰጠው ትኩረት የሚደነቅና የሚበረታታ መሆኑን ገልጻለች።

መንግስት የባሕር በር ማግኘትን የሕልውና ጉዳይ ማድረጉን በመደገፍ የድርሻችን መወጣት ይጠበቅብናል ብላለች።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ብርሃኑ አበበ በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥር ብዛት፣ ቀጣናዊ አዋሳኝነቷ፣ ሕጋዊ ማዕቀፎችና ታሪካዊ ዳራዎች የባሕር በር የመጠቀም መብት እንዳላት የተረጋገጠ ነው ብሏል።

በዚህም የተጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ይበልጥ በማጠናከር በሕጋዊ መንገድ የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን መረባረብ ይገባናል ነው ያለው።

የባሕር በር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ይበልጥ በማነቃቃት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሶ፤ ለወጣቶችና ሴቶች የስራ እድል በመፍጠርም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ያሳድጋል ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሳባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ የቀይ ባሕር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን ማንሳታቸው ይታወሳል።

እንደ ሀገር የባሕር በር አጀንዳ ወሳኝ መሆኑን በማመን ይሕን ለማሳካትም አስፈላጊው ሁሉ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም