ቀጥታ፡

በሻምፒዮንስ ሊጉ ማንችስተር ሲቲ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ ዘጠኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በኢትሃድ ስታዲየም ማንችስተር ሲቲ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠቃሽ ነው። 

ቦሩሲያ ዶርትሙንድ እና ማንችስተር ሲቲ በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ስምንተኛ እና ዘጠነኛ ደረጃን ይዘዋል።

ክለቦቹ በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ዶርትሙንድ አንድ ጊዜ አሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በጨዋታዎቹ ማንችስተር ሲቲ ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር ዶርትሙንድ አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ዶርትሙንድ ሲቲን ያሸነፈው እ.አ.አ በ2012/13 የውድድር ዓመት ሲሆን በምድብ ተገናኝተው 1 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ የተገናኙት እ.አ.አ በ2022/23 ነው። በወቅቱ ባደረጉት ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። 

ቡድኖቹ ባለፈው የውድድር ዓመት ከነበራቸው ደካማ ብቃት በማገገም ዘንድሮ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛል። በዛሬውም ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

የ44 ዓመቱ ፖላንዳዊ ሲሞን ማርሲኒያክ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በሌሎች መርሃ ግብሮች ክለብ ብሩዥ ከባርሴሎና፣ ቤኔፊካ ከባየር ሌቨርኩሰን፣ ኢንተር ሚላን ከካይራት አልማቲ፣ ማርሴይ ከአትላንታ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከአትሌቲኮ ቢልባኦ እና አያክስ ከጋላታሳራይ በተመሳሳይ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ካራባግ ከቼልሲ እና ፓፎስ ኤፍሲ ከቪያሪያል ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም