ቀጥታ፡

በዞኑ የተዘረጋው የቀበሌ አደረጃጀት የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እያገዘ ነው

አዳማ፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ሸዋ ዞን የተዘረጋው የቀበሌ አደረጃጀት ህብረተሰቡ የመንግስት አገልግሎቶችን በቅርበት እንዲያገኝ ከማስቻል ባለፈ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እያገዘ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አባቡ ዋቆ ገለፁ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ህዝቡን በቅርበት በማገልገል አዲስ የቀበሌ አደረጃጀት ዘርግቶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በቅርቡ በተካሄደው የክልሉ መንግስት የሩብ ዓመት አፈጻጸም ላይ የቀበሌ አደረጃጀቶቹ በትክክል የኢኮኖሚ ሽግግር የሚረጋገጥባቸው ማዕከላት እየሆኑ መምጣታቸውን አንስተዋል።

እስካሁን ባለው እንቅስቃሴ የቀበሌ አደረጃጀቶች ህዝቡ አገልግሎት የሚሰጠው፣ ልማት የሚያሳልጥለት አስተዳደር በቅርበት እንዲያገኝ ማድረግ አስችሏል ሲሉም ተናግረዋል።

በዚሁ መነሻነት ኢዜአ ያነጋገራቸው የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደሪ አባቡ ዋቆ እንደገለፁት የቀበሌ አደረጃጀቱ የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎትና የልማት ጥያቄዎችን በቅርበት ለመመለስ ትልቅ እገዛ እያደረገ ነው።

በተለይም ከዚህ ቀደም የገጠሩ ህዝብ ከመሬት፣ ከፍትህና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዘ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ወረዳና ከተማ በመመላለስ አላስፈላጊ ወጪ እና የስራ ጊዜን የሚሻማ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር።

የቀበሌ አደረጃጀቶቹ የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በዚህም በህዝብና በባለሃብቶች ተሳትፎ እንዲሁም በመንግስት አቅም የቀበሌ ጽሕፈት ቤቶች ግንባታን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የቀበሌ መዋቅሩ ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች ባሻገር ዘላቂ ሰላምና ጸጥታ ለማስፈንም ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸው በዚህ ወቅትም ዞኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ወቅትም በተለያየ ምክንያት በ59 ቀበሌዎች ጉዳት የደረሰባቸው የመብራት እና የመሰረተ ልማት ተቋማት ጥገና ተደርጎ ወደ አገልግሎት ተመልሰዋል ነው ያሉት።

በተመሳሳይም የቀበሌ አደረጃጀቱ የገቢ አሰባሰብ አቅምን ለማሳደግ እያገዘ መሆኑን አንስተው በገጠሩ አካባቢ የቤተሰብ ብልፅግናን ለማረጋገጥ መሰረት እየጣለ መሆኑንም ተናግረዋል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን የተደራጁ 302 ቀበሌዎች ያሉ ሲሆን በእነዚህ ቀበሌዎች የተሟላ የሰው ሀይል ተመድቦ ግብዓት የማሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም