ቀጥታ፡

ማዕከላቱ በመዲናዋ የምርት አቅርቦትና ፍላጎትን በማመጣጠን የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር አስችለዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፡-በአዲስ አበባ የተገነቡ የንግድ ማዕከላት የምርት አቅርቦትና ፍላጎቱን በማመጣጠን የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ።

በአዲስ አበባ ሸማችና ነጋዴውን ማገናኘት የሚያስችሉ ግዙፍ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን ማዕከላቱ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን ጨምሮ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት እያቀረቡ ይገኛሉ።


 

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጸጋየ ደበሌ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በአዲስ አበባ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋትና የምርት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በመዲናዋ የተለያዩ ቦታዎች ግዙፍ የገበያ ማዕከላት መገንባታቸውን ጠቅሰው፤ ማዕከላቱ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

በገበያ ማዕከላቱ የሚቀርቡ ምርቶች ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንዳላቸው አመልክተዋል።

ከገበያ ማዕከላቱ በተጨማሪ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ገበያን በማረጋጋት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በገበያ ማዕከላቱ ሲገበያዩ ያገኘናቸው ፍቅሬ ድርሻ የሚፈልጉትን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ መገብየታቸውን ተናግረዋል።

ፈቲያ አሚኑ በበኩሏ በማዕከሉ ለገበያ የቀረቡ ምርቶች ውጭ ከሚሸጡበት ዋጋ  ሰፊ ልዩነት እንዳላቸው ገልጻለች።


 

የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶቹ ከአምራቾች በቀጥታ ለሸማቾች መቅረባቸው ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ  እንዲያገኙ ዕድል መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ ደረጀ ሀይሉ ናቸው።


 

በገበያ ማዕከሉ ምርቶቻቸውን ከሚያቀርቡ አምራቾች መካከል ጉርሙ ጨልቀባ የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር ምርታቸውን በቀጥታ ለሸማቹ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመዲናዋ አራቱም ማዕዘናት በሚገኙ የገበያ ማዕከላት በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው ምርት እያቀረቡ መሆኑን  የገለፁት አቶ ሄኖክ መንግስቱ የተባሉ አምራች ናቸው።


 

ሌላኛው አምራች አቶ አለማየሁ ራጎ በበኩላቸው መንግስት ለአምራቹ የመስሪያ ቦታ ማመቻቸቱ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች እንዲደርሱ ዕድል መፍጠሩን አስታውቀዋል።


 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም