ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የልማት ጉዳዮች ያለልዩነት የምንሰራባቸው የጋራ አጀንዳችን ናቸው-የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

ወላይታ ሶዶ ፤ጥቅምት 26/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የልማት ጉዳዮች ያለልዩነት በመግባባት የምንሰራባቸው የጋራ አጀንዳችን ናቸው ሲሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በብዙ ጫናዎች ውስጥ ሆና በህዝብና መንግስት ጽናትና ቁርጠኝነት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በማሳካት አሁን ላይ ፊቷን ወደ ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች አዙራለች።

ከግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችም ባለፈ የባህር በር በማጣት በታሪክ የደረሰባትን ስብራት ለመጠገን የመልካአ ምድርን፣ የህግን፣ የታሪክንና የመብት ጥያቄዎችን በማንገብ የባህር በር ባለቤት ለመሆን እየሰራች ትገኛለች።

በዚህ ጥረት ውስጥ የለውጡ መንግስት የባህር በር የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑን በጽኑ በማመን ለተግባራዊነቱ ጠንካራ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑ የሚታወቅ ነው። 

በሀገር ልማትና ብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ የመንግስት ጥረት እንዳለ ሆኖ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና እና ተሳትፎ ምን ይመስላል በማለት የኢዜአ ሪፖርተር የተለያዩ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሯል።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹም የፖለቲካ እሳቤ ልዩነት ቢኖራቸውም በሀገር ብሔራዊ ጥቅምና በልማት ጉዳዮች ላይ  የማይደራደሩ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ያለልዩነት ትኩረት ሰጥተን የምንሰራባቸው የጋራ አጀንዳችን ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

በሕብር ኢትዮጵያ ፓርቲ የደቡብ ኦሞ እና አሪ ዞን ቅርንጫፍ ሰብሳቢ አለማየሁ መኮንን፤ በሀገር ጥቅምና የልማት ጥረቶች ላይ እንቅፋት ሆኖ መገኘት የታሪክ ተወቃሽ፤ የህግም ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም በሀገሪቷ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ከዳር እንዲደርሱ እና ብሔራዊ ጥቅምን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የተለየ አቋም ሊኖረን አይችልም ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረጉ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የወደፊቷን ኢትዮጵያ እጣ ፋንታ የሚወስኑ በመሆናቸው ለልጆቻችንና ለቀጣዩ ትውልድ ስንል ለስኬታቸው እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል። 

በሀገር ብሔራዊ ጥቅም፣ በሰላምና በልማት ጉዳዮች ላይ የፓርቲያቸው የማይናወጥ አቋም እንዳለውም ተናግረዋል።

የወላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወህዴግ) ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሚልክያስ ሳንታ፤ በሀገር ጥቅምና በልማት ጉዳይ ላይ በተቃርኖ መቆም ተገቢነት የሌለው መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖሊሲ እና በፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ ልዩነት ቢኖረንም በሀገር ህልውና ጉዳይ ላይ ግን በፍፁም ልንለያይ አንችልም ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም