ቀጥታ፡

የፋብሪካው መገንባት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያግዛል - ኮርፖሬሽኑ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 26/2018(ኢዜአ)፡- የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።

የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ መገንባት ዘርፈ-ብዙ ጥቅም እንዳለው የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽንና ማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራ አመራር ሥራ አስኪያጅ ጋሻው አይችሉህም ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም በዩሪያ ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ከጊዜ፣ ከቦታ ርቀት፣ ከዋጋ፣ ከጥራት ወዘተ አኳያ ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።

እንዲሁም እየጨመረ የመጣውን የአርሶ አደር እና በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች የዩሪያ ማዳበሪያ ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያግዝ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ለዩሪያ አፈር ማዳበሪያ ግዥ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስቀርም ጠቁመዋል።

የግብርና ዘርፍን በይበልጥ በማሳደግ ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን በስፋት ማምረት እንደሚያስችል ገልጸው፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በግብርናው ዘርፍ የውጭ ገበያ ተወዳዳሪነትን በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ያደርጋል ብለዋል።

የዩሪያ ማዳበሪያ በሚፈለግበት ጊዜ፣ ዋጋ እና መጠን በቅርበት ለማግኘት ማስቻሉም ሌላኛው ትሩፋት መሆኑን ነው የጠቀሱት።

የፋብሪካው መገንባት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣትም ይጠቅማል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መስከረም 22 ቀን 2018ዓ.ም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባውን የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።

በ40 ወራት ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው ይህ ፋብሪካ በዓመት 3 ሚሊየን ቶን የማምረት ዐቅም እንዳለውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም