በሻምፒዮንስ ሊጉ ተጠባቂ ጨዋታዎች ሊቨርፑል ሪያል ማድሪድን ባየር ሙኒክ ፒኤስጂን አሸንፈዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሻምፒዮንስ ሊጉ ተጠባቂ ጨዋታዎች ሊቨርፑል ሪያል ማድሪድን ባየር ሙኒክ ፒኤስጂን አሸንፈዋል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ማምሻውን ሰባት ጨዋታዎች ተደርገዋል።
በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አሌክሲስ ማካሊስተር በ61ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
በጨዋታው ሊቨርፑል በርካታ የግብ እድሎችን ቢፈጥርም በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ያሳየው የሪያል ማድሪድ ግብ ጠባቂ ቲቦ ኮርቶዋ አድኗቸዋል።
የቀድሞው የሊቨርፑል ተጫዋች ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ ተቀይሮ በመግባት ያደገበትን ክለብ ገጥሟል።
ውጤቱን ተከትሎ ሊቨርፑል በውድድሩ ሶስተኛ ድሉን ሲያስመዘግብ ሪያል ማድሪድ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
በፓርክ ደ ፕሪንስ ስታዲየም በተደረገው ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ ባየር ሙኒክ የወቅቱን የውድድሩን አሸናፊ ፒኤስጂን 2 ለ 1 አሸንፏል።
ሉዊስ ዲያዝ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥሯል። ዲያዝ በጨዋታው በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ጆአኦ ኔቬስ ለፒኤስጂ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የባሎን ዶር አሸናፊው ኡስማን ዴምቤሌ ባጋጠመው ጉዳት በ25ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።
ባየር ሙኒክ ነጥቡን ወደ 12 ከፍ በማድረግ መሪነቱን ከአርሰናል ተረክቧል። ፒኤስጂ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
በሌሎች ጨዋታዎች ቶተንሃም ሆትስፐርስ ኤፍሲ ኮፐንሃገንን 4 ለ 0 እና አትሌቲኮ ማድሪድ ዩኒየን ሴይንት ጊሎስን 3 ለ 1 አሸንፈዋል።
ሞናኮ ቦዶ ግሊምትን በተመሳሳይ 1 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።
ጁቬንቱስ ከስፖርቲንግ ሊዝበን፣ ኦሎምፒያኮስ ከፒኤስቪ አይንድሆቨን በተመሳሳይ አንድ አቻ ተለያይተዋል።