ቀጥታ፡

በዞኑ የተጀመረውን የሥርዓተ ምግብ ሞዴል መንደር ምስረታ ለማስፋፋት ይሰራል

ደብረ ብርሃን፤ጥቅምት 25/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተጀመረው የሥርዓተ ምግብ ሞዴል መንደር ምስረታ ውጤታማ በመሆኑ ወደሌሎች ዞኖች ለማስፋፋት እንደሚሰራ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። 

በዞኑ አንጎለላና ጠራ ወረዳ የስርዓተ ምግብ ሞዴል መንደር ምርቃትና የስንዴ ክላስተር ልማት የመስክ ምልከታ ዛሬ ተካሂዷል።

በቢሮው የሥርዓተ ምግብ ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ሙጬ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የስርዓተ ምግብን በማሻሻል ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠርና እድገትን ለማፋጠን እየተሰራ ነው።

በክልሉ ትርፍ አምራች በሆኑ ወረዳዎችና ዞኖች ጭምር በአመለካከት ምክንያት የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚስተዋል አስታውሰዋል።

ይሄን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት በሰሜን ሸዋ ዞን የተጀመረው የሥርአተ ምግብ ሞዴል መንደር ምስረታ ውጤታማ በመሆኑ ወደሌሎች ዞኖች ተሞክሮውን ለማስፋት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ታደሰ ማሙሻ በበኩላቸው እንዳሉት ስርዓተ ምግብን በማሻሻል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በዚህም በሰባት ወዳዎች 4 ሺህ 200 እናቶችን በስርዓተ ምግብ ፕሮግራም በማቀፍ ስርአተ ምግብን የሚያሻሽሉ ምርቶችን እንዲያመርቱና ልጆቻቸውን እንዲመግቡ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በአንጎለላና ጠራ ወረዳ ጎልባ ቀበሌ 60 እናቶች የስርዓተ ምግብ መስፈርትን አሟልተው በመገኘታቸው ዛሬ መመረቃቸውንም ተናግረዋል።

የተመረቁት እናቶች አትክልት፣ እንቁላል፣ ወተትንና በንጠረ ነገር የበለጸጉ የምግብ አይነቶችን አምርተው በመጠቀም ያላቸውን ልምድ ለሌሎች ወረዳዎች እንዲያካፍሉ ይደረጋል ብለዋል።

የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደረሰ ደመመ በአስተሳሰብ ችግር ምክንያት አርሶ አደሮች በሴፍትኔት ፕሮግራም ሲረዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ የአመለካከት ለውጥ በማድረግ ካመረቱት ምርት ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ ጤናማና አምራች ትውልድ ለመገንባት እያደረጉት ያለው ጥረት ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል።

ከፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ጀማው እንደገለጹት በጓሯቸው አትክልት ማልማታቸውና ዶሮና ላሞችን ማርባታቸው ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ ለመስጠት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

ይህም ሕፃናት ጤናቸው እንዲጠበቅ፣ ጠንካራ እንዲሆኑና በትምህርታቸውም ውጤታማ እየሆኑ እንዲመጡ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ወይዘሮ ማርታ ሸንቁጤ በበኩላቸው በባለሙያዎች የሚሰጣቸውን የክህሎት ትምህርት ተጠቅመው የቤተሰባቸውን የአመጋጋብ ሥርአት በማሻሻላቸው የልጆቻቸው የእድገትና የጤና ሁኔታ መሻሻሉን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም