ኢትዮ-ኮደርስ የዜጎችን ዓለም አቀፍ የዲጂታል ተወዳዳሪነት በማሳደግ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ ሚና እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ-ኮደርስ የዜጎችን ዓለም አቀፍ የዲጂታል ተወዳዳሪነት በማሳደግ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ ሚና እየተወጣ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮ-ኮደርስ የዜጎችን ዓለም አቀፍ የዲጂታል ተወዳዳሪነት በማሳደግ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቁልፍ ሚና እየተወጣ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮ-ኮደርስ ተነሳሽነት ዜጎች የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበትን ምኅዳር እየፈጠረ የሚገኝ ሀገር አቀፍ የዲጂታል ኢትዮጵያ ልማት መርሃ ግብር አካል መሆኑ ይታዎሳል።
በ5-ሚሊየን የኢትዮ-ኮደርስ ተነሳሽነት የተጀመረው መርሃ ግብርም ዜጎች መሠረታዊ ዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት የሚያዳብሩበትን የበይነ-መረብ (ኦንላይን) የስልጠና ምኅዳር ፈጥሯል።
በተነሳሽነቱም በፕሮግራሚንግ፣ በዳታ ሳይንስ፣ በአንድሮይድና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የስልጠና መስኮች ዜጎች ያለምንም ክፍያ ባሉበት ቦታ በበይነ-መረብ የስልጠና እንዲከታተሉ እያደረገ ይገኛል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተቀዳው የኢትዮ-ኮደርስ ተነሳሽነትም ዜጎች በዲጂታል ዓለም ውስጥ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ብልጽግና ማረጋገጥ የሚያስችል ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ ስዩም መንገሻ፤ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች የመንግስትን አገልግሎቶች በማሳለጥ ተጨባጭ ስኬት እያስመዘገቡ ነው ብለዋል።
የ5-ሚሊየን የኢትዮ-ኮደርስ ተነሳሽነት ስልጠናም ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተቀዳ ቁልፍ የዜጎች ዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት ልማት መርሃ ግብር መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮ-ኮደርስ ተነሳሽነት ስልጠናም በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ ማህበረሰብ በመገንባት በቁልፍ መሳሪያነት እያገለገለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኮደርስ ስልጠና ከጀመረበት አንስቶም በፕሮግራሚንግ፣ አንድሮይድ፣ ዳታ ሳይንስና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረታዊያን ላይ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች ስልጠናውን እየወሰዱ ነው ብለዋል።
በኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና እየተከታተሉ ከሚገኙ ዜጎች ውስጥም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚሆኑት ስልጠናውን አጠናቀው ሰርትፊኬት መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።
የኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብሩም የዜጎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን እያሳደገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ የሰው ሃይል በማፍራት አገልግሎት አሰጣጦችን በማዘመን በር እንደከፈተም ገልጸዋል።
በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት መጨረሻም የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የወሰዱ ዜጎችን 4 ሚሊየን ለማድረስ ከክልልና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያዊያንም የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠናን ባሉበት ቦታ በመመዝገብ የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት አቅማቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።