በበጋ መስኖ ለገበያ ጭምር የሚቀርብ ስንዴ በማምረት ተጠቃሚ ሆነናል- አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በበጋ መስኖ ለገበያ ጭምር የሚቀርብ ስንዴ በማምረት ተጠቃሚ ሆነናል- አርሶ አደሮች
ጎንደር ፤ ጥቅምት 25/2018(ኢዜአ) ፡- በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለገበያ ጭምር የሚቀርብ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
በዞኑ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ዛሬ በወገራ ወረዳ ባልደርጌ ቀበሌ ተካሂዷል።
ከቀበሌው ነዋሪዎች ውስጥ አርሶአደር ተሾመ ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከጀመሩ ሶስት ዓመት እንደሆናቸው ተናግረዋል።
በዚህም ሲያገኙት የቆየው ምርት ከፍጆታቸው የተረፈውን ለገበያ በማቅረብ የልጆቻውን የትምህርት ወጪ በመሸፈን ጭምር ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ይህንን ለማስፋትም በዘንድሮው የበጋ ወቅት ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በበጋ መስኖ የስንዴ ሰብል ለማዋል የእርሻ ስራ መጀመራቸውን አንስተዋል።
ሌላው የቀበሌው አርሶአደር ተስፉ ሙጨ፤ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተሳተፉ እያገኙ ካሉት ትርፍ ምርት ሽያጭ የገቢ አቅማቸው እያደገ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በስንዴ ልማቱ ባገኙት ተጨማሪ ገቢ አንድ በሬ መግዛት እንደቻሉ አውስተዋል።
በዘንድሮ በጋም ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን በሰንዴ ሰብል በመሸፈን 20 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል። ።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የስራ ባሕላችንን በመቀየር የድሕነት መውጫ መንገድ ሆኖናል ያሉት ደግሞ ሌላው አርሶ አደር አስረስ መላኩ ናቸው።
ከመኸር እርሻ በተጨማሪ በጋውን በመስኖ ስንዴ በማልማት ያገኙት ትርፍ ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታችን እንዲጨምር ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልናል ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ በበኩላቸው ፤ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 20ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ780 ሺህ ኩንታል በላይ ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ምርታማነቱን ለማሳደግም ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ የስንዴ ዘር የማቅረብ ስራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ከ6ሺህ በላይ ነባርና አዲስ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አስረድተዋል።
የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያግዙ ሌሎች የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች በስፋት ለመተግበር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ ማስጀመሪያ መረሃ ግብር ላይ አርሶ አደሮችን ጨምሮ የዞኑና የወረዳው አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።