የአፍሪካ ሀገራት የብዝሃ ህይወት ጥበቃን የልማት አጀንዳቸው የትኩረት ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል- ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሀገራት የብዝሃ ህይወት ጥበቃን የልማት አጀንዳቸው የትኩረት ማዕከል ሊያደርጉ ይገባል- ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሀገራት የብዝሃ ህይወት ጥበቃና እንክብካቤን እንደ ልማት አጀንዳ በመያዝ መስራት እንደሚገባቸው የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ ገለጹ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ የብዝሃ ህይወት ጉባኤ በቦትስዋና ጋቦሮኒ ከጥቅምት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
ጉባኤው ላለፉት ሁለት ቀናት በባለሙያዎች ደረጃ ሲከናወን ቆይቶ ዛሬ በሚኒስትሮች ደረጃ ተካሂዷል።
“የብዝሃ ህይወትን በዘላቂነት በመጠቀም የአፍሪካን ብልጽግና ማረጋገጥ” በመሪ መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ያለው ጉባኤ በአፍሪካ ብዝሃ ህይወት ሀብቶች፣ እድሎች፣ ፈተናዎችና ቀጣይ እርምጃዎች የሚመክር ነው።
የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት ከጸጋ ባሻገር የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ እድገት፣ የምግብ ዋስትና እና የባህል ማንነት መሰረት መሆኑን አመልክተዋል።
ብዝሃ ህይወት እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች የዓለም ተፈጥሮ ሀብት ዘቦች ሆነው እያገለገሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥ፣ የእንስሳትና እጽዋት መኖሪያ ቦታ መውደም እና የተለያዩ ዝርያዎች መጥፋት የብዝሃ ህይወት ሀብቶች አደጋ ላይ እንዲወድቁ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካውያን ብዝሃ ህይወትን የአህጉሪቱ የልማት አጀንዳ ምሰሶ መሆኑን በመገንዘብ አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ቁርጠኝነታቸውን ሊያሳዩ ይገባል ነው ያሉት።
በአጀንዳ 2063 የበለጸገች እና ሰላማዊ አፍሪካን የመፍጠር ህልም ሊሳካ የሚችለው በዜጎች ትጋትና በዘላቂ አካባቢ ጥበቃና አስተዳደር መሆኑንም አመልክተዋል።
አህጉራዊ አጀንዳዎችን ለማሳካት የፖሊሲ ማዕቀፎችን ማጠናከር፣ በተፈጥሮ መፍትሄዎች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ እንዲሁም ወጣቶችና ሀገር በቀል ማህበረሰቦችን በብዝሃ ህይወት ጥበቃ የመሪነት ሚና እንዲወጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሀገራት ንግግራቸውን ወደ ተጨባጭ ስራ እና ወደሚለካ ውጤት በመቀየርና የአካባቢ ስነ ምህዳርን በመጠበቅ መጻኢውን ጊዜ የተሻለ ለማድረግ እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።
አፍሪካን በዓለም የብዝሃ ህይወት ጥበቃ እና ዘላቂ አጠቃቀም መሪ እናድርጋት፣ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ነገር እናስረክብ ሲሉም ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በጉባኤው ላይ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች፣ የዓለም የብዝሃ ህይወት ጥበቃ መሪዎች እና ተመራማሪዎች፣ ሀገር በቀል የማህበረሰብ መሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ የብዝሃ ህይወት ጉባኤ ነገ በመሪዎች ደረጃ በሚደረግ ስብሰባ ይጠናቀቃል።
ጉባኤው ለአፍሪካ ብዝሃ ህይወት መመናመን፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ብክለት የተቀናጀ አህጉራዊ ምላሽ መስጠት የሚያስችል መድረክ መሆኑን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።