የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሕጋዊና ታሪካዊ ተቀባይነት ያለው ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው - አምባሳደር ጥሩነህ ዜና - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሕጋዊና ታሪካዊ ተቀባይነት ያለው ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው - አምባሳደር ጥሩነህ ዜና
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትን የማስመለስ ጥያቄ ሕጋዊና ታሪካዊ ተቀባይነት ያለው ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ መሆኑን አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ጥቅምት 18/2018 ዓ/ም ማካሄዱ ይታወቃል።
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ያለው ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አካል የነበረውን የባሕር ጠረፍ ለማጣት 30 ዓመት በላይ የወሰደውን ያህል የትግል ታሪክ አሁን ላይ ወደ ባሕር በር ለመመለስ ሌላ 30 ዓመት እንደማይወስድባት አጽንኦት ሰጥተዋል።
የቀይ ባሕር ባለቤትነትን ጥያቄ ለመፍታት የተረጋጋ፣ የሰከነና በውይይት ላይ የተመሰረተ አካሄድ መከተል ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለማጣት የፈጀውን ያህል ለመመለስ አይፈጅም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት መንገድም ሕጋዊና ተቋማዊ መሠረት የሌለው የሚያስቆጭ የብሔራዊ ጥቅም ስብራት አካል መሆኑን አስረድተዋል።
አንጋፋው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት መንገድ ሕጋዊና ታሪካዊ ቅቡልነት የሌለው ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም በፊት በነበረው ታሪኳ የባሕር በር ባለቤትነቷን አስጠብቃ የቆየች ሀገር ብትሆንም በታሪካዊ ጠላቶች ሴራ ከቀይ ባሕር እንድትገለል መደረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚጋልቧቸውና ህጋዊ መሰረት የሌላቸው አካላት ምንም አይነት የህዝብ ምክክር ሳያደርጉ የባሕር በርን ያህል ግዙፍ የብሔራዊ ጥቅም አንኳር ጉዳይ ማሳጣታቸውን አስታውሰዋል።
በህዝብ የተመረጠ ሕጋዊ የመንግስት አስተዳደር ባልነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ ከባሕር በር የተገለለችበት መንገድ ጉልህ ዓለም አቀፍ የሕግ ጥሰት የተፈጸመበት የታሪክ ስብራት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የአሁኑ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም ህዝባዊ መሠረት ያለው የጋራ ተጠቃሚነት መርህን የተከተለ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
በዚህም የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት የማስመለስ አካሄድ በታሪካዊ ዳራ የተደገፈ ሕጋዊ መሠረትና ተቀባይነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
መንግስትም የኢትጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ለማስመለስ እየተከተለ የሚገኘው በሳል የዲፕሎማሲ አካሄድ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከጥንተ አክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ የቀይ ባሕር ቀጣናን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ የባሕሩ ባለቤትና ተጋሪ ሀገር እንደነበረችም ነው አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ያስታወሱት።
በፖለቲካ ሴራ ከአካባቢው እንድትርቅ መደረጉ የቀይ ባህር ቀጣና የአሸባሪዎች መናኸሪያ በመሆን ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት መታወክ መንስኤ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ የሚያሻው ጉዳይ መሆኑና ብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ ባለፈ የቀጣናውን ደኅንነት በማስጠበቅ ለዓለም አቀፍ የሚተርፍ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።
ኢትጵያውያን፣ የቀጣናው ሀገራትና የዓለም ህዝብ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ምክንያታዊ ጥያቄ በጎ ምላሽ እንዲያገኝ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።