ቀጥታ፡

የአውሮፓ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እንዲሳተፉ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል-ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 25/2018(ኢዜአ)፦ መንግስት በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መሰማራት ለሚፈልጉ የአውሮፓ ባለሀብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም በፈረንሳይ ፓሪስ ተካሄዷል።

ኢትዮጵያ በፎረሙ ላይ የልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቿ የኢንቨስትመንት ዘርፉን በማሳለጥ ረገድ እየተወጡት ያለውን ሚና አቅርባለች።

በዘመናዊ ሎጅስቲክስ እና የትራንስፖርት መሰረተ ልማት የተደገፉት የኢኮኖሚ ዞኖች ለባለሀብቶች የአሰራር ሂደቶችን የሚያቀላጥፉ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው የተገነቡ እና የተቀናጁ የኢንዱስትሪ አገልግሎቶችን እንደሚሰጡ ተመላክቷል።

በፎረሙ ላይ ኢትዮጵያ ለባለሀብቶች ምቹ ምህዳርን ለመፍጠር እና የንግድ ስራ ምቹነት ለማሻሻል ያላትን ቁርጠኝነት፣ የህግ ማዕቀፍ ግልጽነትና ተጠያቂነት እና የመንግስት-የግል አጋርነቶች አስመልክቶ ለፎረሙ ተሳታፊዎች ገለጻ ተደርጓል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የኢንዱስትሪ ማዕከላት ብቻ ሳይሆኑ የኢንቨስትመንት፣ ኢኖቬሽን እና ንግድ መግቢያ በሮች ናቸው ብለዋል።

መንግስት መሰረተ ልማትን በማቅረብ፣በመደገፍ እና አጋርነትን በማጠናከር ባለሀብቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ቁርጠኛ መሆኑን አመልክተዋል።

የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሞቱማ ተመስገን ዘመናዊ መሰረተ ልማት፣ ተአማኒነትን ያላቸው መገልገያዎች እና ፍላጎትን ያማከሉ ልዩ አገልግሎቶችን አቀናጅቶ የያዘ መሆኑን አመልክተዋል።

ግባችን ኢትዮጵያን የዘላቂ ኢንቨስትመነት መዳረሻ ማድረግ፣ እድገትን ማረጋገጥ እና ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ባለሀብቶችን ምቹ እድሎችን መፍጠር ነው ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የግሎባል አፍሪካ ሎጅስቲክስ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሃይም ኮንፎርቲ፣ የጀርመን የንግድ ባንክ ኬኤፍደብሊው አይፔክስ ምክትል ፕሬዝዳንት ካሪን ሙልደር እና የዓለም አቀፉ የምህድስና አማካሪ ድርጅት ሲስትራ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ሉዊስ ዴቪድ የዓለም ኢንቨስትመንት አዝማሚያዎች እና ቀጣናዊ የሎጅስቲክስ ልማትን አስመልክቶ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

በፎረሙ ላይ የተሳተፉ የአውሮፓ ባለሀብቶች እና የንግድ መሪዎች የኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በማኑፋክቸሪንግ፣ሎጅስቲክስ እና ንግድ ዘርፍ ያሉ ስትራቴጂካዊ እድሎችን ለማስፋት የሚያግዙ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር እንደሚያጠናክሩም መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም