ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በ "ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ" ማዕቀፍ ሁሉን አቀፍ እድገት እና ልማትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ትሰራለች-የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 25/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአውሮፓ ህብረት "ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ" ኢኒሼቲቭን እድሎችን በመጠቀም ሁሉን አቀፍ እድገት እና ልማትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም በፈረንሳይ ፓሪስ ተካሄዷል።

በፎረሙ ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ የአውሮፓ ህብረት የ“ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ” ኢኒሼቲቭ ነው።

"ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ" በአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን የሚመራ የአውሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ ኢኒሼቲቭ ሲሆን ህብረቱ ከተለያዩ ሀገራት በዲጂታላይዜሽን፣በታዳሽ ኃይል፣በስርዓተ ምግብ፣ በጤና፣ በዘላቂ ግብርና፣ሰላምና ደህንነትን ጨምሮ በቁልፍ ዘርፎች ያለውን ትብብርና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው።


 

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ እና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የአውሮፓ ህብረት እና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢኒሼቲቩ አማካኝነት በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ታዳሽ ኢነርጂ፣ዲጂታል ትስስር እና አረንጓዴ ልማት ሽግግር የኢንቨስትመንት ፍሰትን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ከህብረቱ እና ከባንኩ ተወካዮች ጋር አጋርነትን ማጠናከር በሚቻልባቸው መስኮች ላይ የተወያዩ ሲሆን ኢትዮጵያ ግሎባል ጌትዌይን በመጠቀም ሁሉን አቀፍ እድገት፣ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይገበር ልማትን ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።


 

ውይይቱ ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ ዘላቂ ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር፣የኢኮኖሚ ትስስርን ለማጎልበት እና የረጅም ጊዜ ግንኙነታቸውን ለማጽናት ያላቸውን የጋራ ራዕይ የሚያመላክት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም