ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በኢንቨስትንመንት አማራጮች ተሳታፊ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 25/2018 (ኢዜአ)፡-በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በሀገር ልማትና ኢንቨስትንመንት አማራጮች ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት መደረጉን በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ገለፁ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ዳያስፖራው ያለውን ሀብትና እውቀት ተጠቅሞ ለሀገር ኢኮኖሚ፣ የገፅታ ግንባታ እንዲያውል መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በእንግሊዝ እና ሰሜን አየርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ልማትና በተለያዩ ዘርፎችን ድጋፎች እያደረጉ ይገኛሉ።


 

ኤምባሲው ከዳያስፖራው ጋር በመቀናጀት ለሀገሪቱ ልማትና ዕድገት መሠረት የሚሆኑ ስራዎችን በማከናወን ረገድ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ለማስቻል ሲሰራ መቆየቱንም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከፋይናንስ ድጋፍ ባለፈ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ረገድም የበኩሉን መወጣቱን ተናግረዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ ዳያስፖራው ያለውን ሀብትና እውቀት ተጠቅሞ ለሀገር ኢኮኖሚ፣ የገፅታ ግንባታ እንዲያውል መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን አመላክተዋል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምን ተከትሎም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በኢንቨስትመንትና ንግድ ዘርፎች ተሳታፊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሪፎርሙ ኤምባሲው በሚሸፍናቸው አካባቢዎች ያሉ የቢዝነስ ኮሙዩኒቲ በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዱባይና ሰሜን ኤምሬትስ የኢፌዴሪ ቆንሱል ጄኔራል ፅህፈት ቤት ተጠባባቂ ጉዳይ ፈፃሚ አስመላሽ በቀለ፥ ፅህፈት ቤቱ በኢምሬቶችን ለሚገኙ በርካታ ዜጎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።


 

በዱባይና ሰሜን ኢምሬቶች ያሉ ዜጎች በሀገራቸው ልማት የላቀ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ማህበር ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት ለልማት ስራዎች የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ለማህበራዊ ዘርፍ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም አቅመ ደካሞችን ሲደግፉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በአገር ደረጃ የሚተገበሩት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለመደገፍ የሚያስችሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ በበኩላቸው፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሀገር ልማት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያደረጉ ናቸው ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት፣ የከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውና በመንግስት የተወሰዱ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ሌሎችንም ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ተናግረዋል።

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፍ ሁኔታ መመቻቸቱን ጠቁመው፥ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የይቻላል መንፈስን በመያዝ ወደሌሎች የልማት ስራዎች መገባቱን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም