ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ2 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ2 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና እየሰጠ ነው
ደሴ ፤ጥቅምት 25/2018 (ኢዜአ)፦በደሴ ከተማ የሚገኘው ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ2 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።
የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ እንደገለጹት፣ ሆስፒታሉ በዓይን ሞራ ግርዶሽ የተጠቁ ወገኖችን ለማገዝ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ሕክምና መስጠት ጀምሯል።
በአገልግሎቱ ከደቡብ ወሎ፣ ከሰሜን ወሎ፣ ከዋግኽምራ ብሔረሰብ፣ ከኦሮሞ ብሔረሰብ እንዲሁም ከሰሜን ሸዋ ዞኖችና አጎራባች ክልሎች ለሚመጡ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ሕክምናው ከኪውር ብላይንድነስ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር እየተሰጠ ሲሆን የታካሚዎች የትራንስፖርትና የምግብ ወጪ በመሸፈን ሕክምናውን እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የሆስፒታሉ የዓይን ሕክምና ክፍል ኃላፊና የነጻ ሕክምናው አስተባባሪ አቶ እንዳልክ ያረጋል፤ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ብዙውን ጊዜ በዕድሜ መግፋት የሚከሰት የጤና ችግር መሆኑን አንስተው፣ በወቅቱ ካልታከመ ለዓይነ ስውርነት እንደሚዳርግና ሆስፒታሉም ይህን ለመታደግ በዘመቻ ነጻ ቀዶ ሕክምና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀን እስከ 400 ሰዎች ሕክምናውን እንደሚያገኙ ጠቁመው፤ ለዚህም 9 የዘርፉ ስፔሻሊስት ዶክተሮችን ጨምሮ ከ100 በላይ የዓይን ሐኪሞችና ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የነጻ ሕክምናው ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አቶ ተሾመ እሸቴ በሰጡት አስተያየት ለዓመታት የዓይን ብርሃናቸውን በማጣታቸው ተቸግረው ቆይተዋል።
በሆስፒታሉ በተደረገላቸው ሕክምና ሁለቱም ዓይኖቻቸው ማየት በመጀመራችው መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ "እየተመራሁ መጥቼ እራሴን ችዬ መንቀሳቀስ ጀመርኩ" ብለዋል።
ሌላኛዋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ መሬማ ማህሙድ በበኩላቸው፣ በሕክምናው የሁለቱም ዓይኖቻቸው ሙሉ ብርሃን በመመለሱ ዳግም የተወለዱ ያህል ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታሉ ባለፉት ዓመታት በዘመቻ ብቻ 19ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ነጻ የዓይን ሞራ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።