ቀጥታ፡

በጂንካ ከተማ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 280 የንግድ ድርጅቶች አስተዳደራዊ እርምጃ ተወሰደባቸው

ጂንካ፤ጥቅምት 25/2018 (ኢዜአ)፦በጂንካ ከተማ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 280 የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

በከተማዋ በምርቶች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭምሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመላክቷል።

የአስተዳደሩ የንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ባይስማይ ለኢዜአ እንዳሉት በከተማው ምክንያዊ ባልሆነ መንገድ በምርቶች ላይ ዋጋ በሚጨምሩ አካላት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ ነው።

የከተማው የቁጥጥር ግብረ ኃይል ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ 280 የንግድ ድርጅቶች የደመወዝ ማሻሻያውን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ  ማድረጋቸውን  አረጋግጧል ብለዋል።

በዚህም ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ፣ ምርት በመሸሸግ ሰው ሰራሽ እጥረት በፈጠሩ፣ ያለ ንግድ ፍቃድ በሚሰሩ እና ከዘርፍ ውጪ በሚነግዱ  ህገወጦች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።

ከእነዚህም ቀላል ጥፋት ፈጽመው ለተገኙ 130 የንግድ ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን በቀሪዎቹ ድርጅቶች ላይ  የገንዘብና የንግድ ፍቃድ እስከ መሰረዝ የደረሰ ቅጣት መጣሉን ተናግረዋል።

አስተዳደሩ የቁጥጥር ስራውን እንደሚያጠናክር ገልጸው ህብረተሰቡም በንግድ ድርጅቶች በተለጠፈው ዋጋ እንዲስተናገድና ከተጠቀሰው ዋጋ በላይ የሚጠይቁ ሲኖሩ ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።


 

የከተማው ነዋሪ አቶ ቦጋለ ምትኩ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ በህገወጦች ላይ የሚያደርገውን ክትትል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀው የንግድ ድርጅቶችም በአቋራጭ ለመበልፀግ ከሚደረግ ኢ-ሞራላዊ ድርጊት በመቆጠብ በታማኝነት ህብረተሰቡን ማገልገል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

በከተማው በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ራህመት ሱሌይማን፤ የደመወዝ ጭማሪና ሌሎች ምክንያቶችን በመፍጠር  የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ አግባብነት የለውም ብለዋል።


 

በተለይ በጅምላ አከፋፋዮች ላይ የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም