ቀጥታ፡

የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ መዘመን እንግልትን አስቀርቶልናል-  ተገልጋዮች

አርባ ምንጭ ፤ጥቅምት 25/2018 (ኢዜአ)፦ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል  አገልግሎት አሰጣጥ መዘመን እንግልትን በማስቀረት የተገልጋዩን እርካታ እያሳደገ መሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተገልጋዮች እንደገለፁት፤ የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል እየሰጠ ያለው ከወረቀት ንክኪ ነፃ አገልግሎት የተገልጋዩን ማህበረሰብ እንግልት ማስቀረት አስችሏል። 

ከሆስፒታሉ ህክምና ተገልጋዮች መካከል ከቡርጂ ዞን የመጡት አቶ ደበበ ጮታ በሆስፒታሉ የረጅም ግዜ ተገልጋይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ በሚመጡበት ወቅት የአገልግሎት አሰጣጡ መዘመን የተገልጋይን የጊዜና የገንዘብ ብክነት ማስቀረት እንዳስቻለ ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ የተገበረው ከወረቀት ንኪክ ነፃ አገልግሎትና የባለሙያዎች ትህትና አስደሳች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ የምስራች ጉጃ  ናቸው።


 

የሆስፒታሉ የአገልግሎት ቅልጥፍና ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው ያደርጉት የነበረን እንግልት ማስቀረቱንና በመድኃኒት አቅርቦት ረገድም መሻሻል መኖሩን ጠቁመዋል። 

የሆስፒታሉ ምድረ ግቢም ውብና ሳቢ መሆኑ  ለታካሚዎች  ተጨማሪ የፈውስ  እቅም እንደሆነም  አስረድተዋል።

በሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያ ዶክተር ወንድይፍራው ከበደ ሆስፒታሉ በህክምና ባለሙያዎችና መሣሪያዎች በበቂ ሁኔታ መደራጀቱን ጠቅሰው ህሙማንን በአክብሮትና በእንክብካቤ እያገለገልን እንገኛለን ብለዋል።


 

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አምባቸው ዱማ በበኩላቸው በሆስፒታሉ የታካሚዎችን እርካታ ይበልጥ ለማሳደግ የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን በማዘመን ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ነፃ  አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ይህም በካርድ ፍለጋና በሌሎች ምክንያቶች ይፈጠር የነበረውን እንግልት ያስቀረ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በተጨማሪም ታካሚዎች ቤታቸው ሆነው የህክምና የምክር አገልግሎትና ቀጠሮ የሚይዙበት ነፃ የስልክ  መስመር መዘጋጀቱን ስረድተዋል።

ሆስፒታሉ የአንጎል ቀዶ ህክምናን ጨምሮ በተለያየ ዘርፍ ስፔሻሊስት የሆኑ ሐኪሞችን የያዘና ኤም አር አይን ጨምሮ በዘመናዊ የህክምና መሣሪያዎች የተደራጀ በመሆኑ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ሌሎች አካባቢዎች  የሚላኩ ታካሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ገልጸዋል።

በአካባቢው በሌሎች ሆስፒታሎች የማይሰጡ የቃጠሎና የኦክሲጅን ህክምናዎች በተጠናከረ ሁኔታ እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በ1961 ዓ.ም  የተመሰረተው  የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል  ከጋሞ፣ ከጎፋ፣ ከባስኬቶ፣ ከጋርዱላ፣ ከኮንሶ፣ ከቡርጂ፣ ከኮሬ፣ ከአሪ እና ከደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም ከከፊል ኦሮሚያ እና ከሲዳማ ክልሎች ለሚመጡ ተገልጋዮች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም