የኢትዮጵያ የስነ-ምህዳር እና ብዝኃ-ሕይወት ጥበቃ ስራዎች ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የስነ-ምህዳር እና ብዝኃ-ሕይወት ጥበቃ ስራዎች ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው
አዲስ አበባ፤ጥቅምት 25/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በስነ-ምህዳር እና ብዝኃ-ሕይወት ጥበቃ የምታከናውናቸው ተግባራት ከቀጣናው ባሻገር ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ምሳሌ መሆናቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የስነ-ምህዳርና ባዮ-ዳይቨርሲቲ ዋና የቴክኒክ አማካሪ ዶለይ ጸሪንግ ገለጹ፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የስነ-ምህዳርና ባዮ-ዳይቨርሲቲ ዋና የቴክኒክ አማካሪ ዶለይ ጸሪንግ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ስነ-ምህዳርና ብዝሃ ህይወት የታደለች ሀገር ናት ብለዋል፡፡
የብዝሃ ህይወት እና ስነ-ምህዳር ጥበቃ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚያበረክት ጠቁመው፤ ተቋማቸው በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከበርካታ የዓለም ሀገራት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በብሔራዊ ፓርኮች ጥበቃን በማጠናከር እና አዳዲስ ስፍራዎችን በማልማት ለብዙ አይነት የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ወሳኝ መኖሪያ እያለማች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በትላልቅ የደን ልማት እያከናወነች ያለው ተግባር ከአፍሪካ ቀንድ አልፎ በዓለም አቀፉ ደረጃ ግንባር ቀደም እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በስነ-ምህዳር እና ብዝሃ ህይወት ጥበቃ ዘርፍ እያከናወነች ያለው ተግባር አስደናቂ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ስራዎች ቀጣዩን ትውልድ ጭምር ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይ ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እና ከብዝኃ-ሕይወት ጥበቃ ጋር ለማስተሳሰር እየወሰደቻቸው ያሉ እርምጃዎች የሚደነቁ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በስነ-ምህዳር እና ብዝኃ-ሕይወት ጥበቃ ረገድ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ከቀጣናው ባሻገር ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ኢትዮጵያ የምታከናውነውን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራን እንደሚያግዝም አረጋግጠዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በቀጣናው የሚገኙትን ሥነ-ምህዳሮችና የብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ ከመንግሥት፣ ከሲቪል ማኅበራት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ከፍተኛ ተመራማሪ (ዶ/ር) ፋኑዔል ከበደ በበኩላቸው፤ የዱር እንስሳት ለቱሪዝም መስህብነትና ለሌሎችም ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ የእነዚህን እንስሳት መኖሪያ የመጠበቅ ስራን በትኩረት እየሰራች መሆኑን ጠቁመው በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
በዚህም በርካታ የዱር እንስሳት አሁን ላይ ወደ ነባር ቀዬያቸው እየተመለሱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡