ቀጥታ፡

የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማሻሻል ምቹ የመማር ማስተማር ምኅዳር ፈጥሯል  

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 25/2018 (ኢዜአ)፦ የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማሻሻል ምቹ የመማር ማስተማር ምኅዳር መፍጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶች ገለጹ።

በ2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተተገበረው የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት መሰረት እየጣለ ይገኛል።

መርሃ ግብሩም ባለፉት ዓመታት ምቹ የመማር ማስተማር ምኅዳር በመፍጠር በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ ስኬት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የቡርቃ ዋዩ ቅድመ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሰ መምህር አዲሱ ግዛው፤ መርሃ ግብሩ በተማሪ ምገባ አገልግሎትና ትምህርት ጥራት ላይ ምቹ የመማር ማስተማር ምኅዳር ፈጥሯል ብለዋል። 


 

መርሃ ግብሩም የህዝብና መንግስትን ትብብር በማጠናከር የትምህርት ቤቶችን ግብዓት በማሟላት በተማሪ ቁጥርና በትምህርት ጥራት ላይ ለውጥ እንዲመዘገብ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የተማሪዎች ውጤት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመዘገብ ማድረጉንም ነው የገለጹት።

የእንጦጦ ማርያም ቅድመ አንደኛ፣ መጀመሪያና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዋና  ርዕሰ መምህር ኢፋ ሀይሌ፤ መርሃ ግብሩ የተማሪዎችን ከክፍል ወደ ክፍል የማለፍ ውጤታማነት እያሻሻለ ነው ብለዋል።


 

በተጨማሪም በመርሃ ግብሩ የቤተ-መጽሐፍትና የምርምር ክፍሎችን የቁሳቁስ ፍላጎት በማሟላት ተማሪዎች ንድፈ ሀሳብን ከተግባር ያቀናጀ ዕውቀት እንዲጨብጡ እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር)፤ የትምህርት ለትውልድ ሀገር አቀፍ መርሃ ግብር ምቹ የመማር ማስተማር ምኅዳርን በመፍጠር ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ ነው ብለዋል።  


 

በቅድመ አንደኛና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ በምገባ መርሃ ግብር፣ መምህራንን በማብቃትና የትምህርት ቤቶችን ቁሳቁስ በማሟላት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን እያሳደገ መሆኑን ተናግረዋል።

የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት በማሟላት በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ጉልህ ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም