የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 25/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት አርባምንጭ ከተማ ከአዳማ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፈም። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። ቡድኑ በሁለት ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው ሶስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ያለ ግብ አቻ በመለያየት በሶስት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላኛው መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ በማግኘት 15ኛ ደረጃን ይዟል።
ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በስድስት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ጨዋታው ንግድ ባንክ የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ የሚያደርጉት ነው።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከመቻል ምሽት 12 ሰዓት ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ያገኘው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
መቻል በሊጉ ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። ቡድኑ በሰባት ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማሳካት ይጫወታል። መቻል ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ዳግም ይረከባል።