ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከይርጋጨፌ ቡና ጋር ያደርጋል 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 25/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከይርጋጨፌ ቡና ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታል።

ንግድ ባንክ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ተሳትፎ ምክንያት የመጀመሪያ ሶስት ሳምንታት ጨዋታዎቹን አላደረገም።

ጨዋታዎቹ በተስተካካይ መርሃ ግብርነት ተይዘዋል። 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግን ስምንት ጊዜ ያሸነፈ ሲሆን ያለፉት አምስት ተከታታይ የውድድር ዓመታት የዋንጫ ባለቤትም ነው። 

ከኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ያደገው ይርጋጨፌ ቡና በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።

ቡድኑ በጨዋታዎቹ ምንም ግብ አላስቆጠረም፣ ምንም ጎል አልተቆጠረበትም። 

በሌላኛው መርሃ ግብር መቻል ከሲዳማ ቡና ከረፋዱ አራት ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሃዋሳ ከተማ በተመሳሳይ ዘጠኝ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በሊጉ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። መቻል በስድስት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም